በማሊው ራዲሰን ብሉ ሆቴል የደረሰውን ጥቃት አቀነባብሯል የተባለው ፍርድ ቤት ቀረበ

ማሊ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ታትሟል

የውጭ ዜጎች ላይ ባነጣጠሩ እና እአአ በ2015 ማሊ ውስጥ ከደረሱ የሽብር ጥቃቶች ጀርባ ነበሩ የተባሉ ሁለት ግለሰቦች በዋና ከተማዋ ባማኮ ፍርድ ቤት ቀረቡ።

ታጣቂዎች በዚያ ዓመት መጋቢት ወር በላ ቴራስ የምሽት ክበብ እና በኅዳር ወር በራዲሰን ብሉ ሆቴል ባደረሱት ጥቃት ቢያንስ 26 ሰዎች ተገድለዋል።

ተጠርጣሪዎች ጥቃቶችን በማቀነባበር እና በማስፈፀም ክስ ተመሰረቶባቸዋል።

ከእአአ 2012 ወዲህ ሠርጎ ገቦችን በመዋጋት ላይ ላለችው ማሊ ችሎቱ ያልተለመደ ነው ተብሏል።

የፈረንሣይ ወታደሮች የማሊ ጦርን ሲረዱ ቢቆዩምም የማሊ መንግሥት ግን አገሪቱን አሁንም ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር አልቻለም።

እንደ ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ከሆነ ከጥቃቶቹ ጀርባ አለበት የተባለው ዋነኛ ተጠርታሪ ሞሪታናዊው ፋዋዝ ኡልድ አህሜይዳ በተሸፋፈኑ ጠባቂዎች ወደ ፍርድ ቤቱ ያቀና ሲሆን ህንጻው ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ በታጠቁ ወታደሮች ጥበቃ ተደርጎለታል።

ዋነኛ ተጠርታሪ ሞሪታናዊው ፋዋዝ ኡልድ አህሜይዳ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ዋነኛ ተጠርታሪ ሞሪታናዊው ፋዋዝ ኡልድ አህሜይዳ

የፈረንሳዩ ጋዜጣ ቻርኪ ሄብዶ የነብዩ መሃመድን አጨቃቻቂ የካርቱን ምስል አትሟል በሚል ተጠርታሪው በምሽት ክበብ ውስጥ በወሰደው የበቀል እርምጃ ሶስት ሰዎችን ገድሏል ተብሏል።

በ2016 በቁጥጥር ስር ዋለው አህሜይዳ የራዲሰን ብሉውን ጥቃትን በማቀነባበርም ተከሷል።

በ2015 ታጣቂዎች በላ ቴራስ ተብሎ በሚጠራ የምሽት ክበብ ላይ ተኩስ ከመክፈት ባለፈ የእጅ ቦምብ ወርውረው ሦስት ማሊያውያን፣ አንድ ፈረንሳዊ እና አንድ ቤልጄማዊ ገድለዋል፡፡

ከስምንት ወራት በኋላ ሁለት ታጠቂዎች በራዲሰን ብሉ ሆቴል 170 እንግዶችንና ሰራተኞችን አፍነው ለዘጠኝ ሰዓታት ቆይተዋል። የፀጥታ ኃይሎች ህንፃውን ከመቆጣጠራቸው በፊት ቢያንስ 20 ሰዎች ሲገደሉ 14ቱን ደግሞ ቆስለዋል።

ዘጠኝ ማሊያውያን፣ የሩሲያ የበረራ ሠራተኞች፣ የቻይና የግንባታ ሥራ አስፈፃሚዎች፣ አንድ የቤልጂየም ፖለቲከኛ እና አንድ አሜሪካዊ የእርዳታ ሠራተኛ ከተገደሉት መካከል ናቸው።

ከእገታ የዳነ አንድ ታዳጊ በወቅቱ የተኩስ ድምፆቹ "ርችቶች" መስለውኝ ነበር ብሏል።