ቺሊያውያን ከፋፍሎናል ያሉትን ሕገ መንግሥት ሊቀይሩ ነው

ሳንትያጎን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ደስታቸውን ለመግለጽ አደባባይ ወጥተዋል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ሳንትያጎን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ደስታቸውን ለመግለጽ አደባባይ ወጥተዋል
ታትሟል

የቺሊ ዜጎች ሕገ መንግሥታቸው እንዲቀየር ድምጻቸውን ሰጥተዋል። ሕገ መንግሥቱ የረቀቀው በአምባገነኑ ጀነራል አውገስቶ ፒንቾት ዘመን ነበር።

እኩልነት እንዲሰፍን የሚጠይቅ የተቃውሞ ሰልፍ መካሄዱን ተከትሎ ሕዝብ ውሳኔ ተካሂዷል። ወደ 90 በመቶ ከሚሆኑ ድምጾች መካከል 78% ሕገ መንግሥቱ ይቀየር ብለዋል።

ፕሬዘዳንት ሰባስሽን ፒኔራ፤ ሰላማዊ የምርጫ ሂደቱን አሞግሰው ውጤቱን ተቀብለዋል። "አብረን መሥራት የምንጀምርበት ጊዜ ነው" ብለዋል።

ቺሊ ውስጥ መንግሥት የሚቃወም ሰልፍ የተጀመረው አምና ነበር። ተቃዋሚዎቹ ካነሷቸው ጥያቄዎች አንዱ፤ በማኅበረሰቡ ዘንድ እኩልነት እንዳይሰፍን እንቅፋት የሆነው ሕገ መንግሥት እንዲለወጥ ነበር።

ፕሬዘዳንቱም "እስካሁን ሕገ መንግሥቱ ከፋፍሎናል። አዲሱ ሕገ መንግሥት አንድነትን እና መረጋጋትን እንዲሰጠን በጋራ መሥራት አለብን" ብለዋል።

ሕዝበ ውሳኔው ሁለት ጥያቄዎች ነበሩት። አንዱ ሕዝቡ አዲስ ሕገ መንግሥት ይፈልጋል? ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ አዲሱን ሕገ መንግሥት ማን እንዲያረቀው ይፈልጋሉ? የሚለው ነው።

አብዛኛው ዜጋ አዲሱ ሕገ መንግሥት በሕዝብ የተመረጡ ሰዎችን በያዘ ቡድን እንዲረቅ ይፈልጋሉ። ሌላኛው አማራጭ ሕገ መንግሥቱ በሕግ አውጪዎች ይረቀቅ የሚል ሲሆን፤ ሕዝቡ ግን ይህንን ሐሳብ አልደገፈም።

ለቺሊያውያን አዲስ ሕገ መንግሥት የአምባገነን ዘመን ማክተሙን ማሳያ ነው። ዴሞክራሲ እንደሚሰፍንም ተስፋ አላቸው።

ምርጫው መካሄዱ የወራት ተቃውሞ ፍሬ እንዳፈራ ቢያሳይም፤ ዜጎች ሕገ መንግሥቱን የሚያረቅ ቡድን የማዋቀር ሥራ ይጠብቃቸዋል።

ሳንትያጎን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ደስታቸውን ለመግለጽ አደባባይ ወጥተዋል።

ሕዝበ ውሳኔው ሚያዝያ ላይ ሊካሄድ ታቅዶ ነበር። ነገር ግን በኮሮናቫይረስ ሳቢያ ተዘዋውሯል።

በቀጣይ ሁለት ዓመታት 155 አባላት ያሉት አዲስ የሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚቴ ይዋቀራል። ኮሚቴው የሚስማማበት አዲስ ሕገ መንግሥት በዓመት ውስጥ አውጥቶ ለሕዝብ ውሳኔ ያቀርባል።

ባለፉት 20 ዓመታት በቺሊ ድህነት በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል። አሁን ላይ በደቡብ አሜሪካ ሀብታሟ አገር ናት። ሆኖም ግን አሁንም በዓለማችን እኩልነት ከማይስተዋልባቸው አገሮች አንዷ ናት።

ብዙዎች የሚወቅሱት አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች በከፊል በግል ባለሀብቶች እጅ እንዲሆኑ ያደረገውን ሥርዓት ነው።

እንዲቀየር የተወሰነው ሕገ መንግሥት የረቀቀው እአአ በ1980 ጀነራል ፒንቾች ሕዝበ ውሳኔ ካደረጉ በኋላ ነበር።

የ17 ዓመቱ ወታደራዊ አገዛዝ በጭቆና፣ እንግልትና ዜጎችን በመሰወር ይኮነናል።