ኮሮናቫይረስ፡ ቺሊ ከኮሮናቫይረስ ላገገሙ "ከቫይረሱ ነፃ" የሚል የምስክር ወረቀት ልትሰጥ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የቺሊ መንግሥት ከኮሮና ቫይረስ ላገገሙ ዜጎች "ከቫይረሱ ነፃ" የሚል የምስክር ወረቀት እሰጣለሁ ማለቱ አወዛጋቢ ሆኗል።
ይህ የምስክር ወረቀትም ወደ ስራ እንዲመለሱ ማስረጃ እንደሚሆናቸውም የአገሪቷ ምክትል የጤና ሚኒስትር ፓውላ ዳዛ ገልፀዋል።
ውሳኔውን የተቹት አካላት በበኩላቸው የምሰክር ወረቀቱ ባዶ ተስፋን ይሰጣል፤ ቫይረሱም የበለጠ እንዲስፋፋ በር ይከፍታልም እያሉ ነው።
ለዚህም እንደ ማስረጃነት የሚጠቅሱት የአለም ጤና ድርጅት ከኮሮናቫይረስ ያገገሙ ሰዎች እንደገና ላለመያዛቸውም ምንም አይነት ዋስትና የለም በማለትም ማስጠንቀቁን በማውሳት ነው።
ከጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ በተገኘው መረጃ መሰረት በቺሊ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 13ሺ ሰዎች ሲሆን፣ 189ም ዜጎቿን በሞት ተነጥቃለች።
"እስካሁን ባለው መረጃ ከኮሮናቫይረስ ያገገሙ ሰዎች እንደገና የመጠቃት እድል የላቸውም የሚል ምንም አይነት መረጃ የለም። በሽታውን የመቋቋም አቅማቸው ይጨምራል የሚልም ማስረጃ የለም" በማለት አለም አቀፉ የጤና ድርጅት ባለፈው ሳምንት አሳውቋል።
ድርጅቱ አክሎም ከበሽታው ነፃ ነው የሚል የምስክር ወረቀት መስጠቱ ህዝቡ በሽታውን ለመከላከል ከሚያደርገው ጥንቃቄ እንዲዘናጋና፤ ነፃ የተባሉትም ሰዎች በሽታውን በከፍተኛ ሁኔታ ሊያስተላልፉ ይችላሉ ብሏል።
የቺሊ ጤና ሚኒስቴር ግን በድርጅቱ ሃሳብ አይስማም፣ በተቃራኒው ፓውላ ዳዛ እንደሚሉት "በኮሮናቫይረስ ተይዞ ያገገመ ሰው ሁለተኛ የመያዝ እድሉ ዝቅተኛ እንደሆነ እናውቃለን" የሚሉት ሚኒስትሯ የምስክር ወረቀቱ ከበሽታው ማገገማቸውን የማሳወቂያ መንገድ እንጂ እንደገና አይያዙም የሚል አይደለም ብለዋል።
የአለም ስጋት በሆነው ኮሮና ቫይረስ ከ200 ሺ ሰዎች በላይ ህይወትን ያጠፋ ሲሆን፤ መንግሥታትም የቫይረሱን ለመዛመት ጥለዋቸው የነበሩ አስገዳጅ መመሪያዎችን ለማላላት መንገዶችን እየቀየሱ ነው።













