የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ለተቃዋሚ ሰልፈኞች የሰላም ጥሪ አቀረቡ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ሙሐመድ ቡሃሪ በንግድ ከተማዋ ሌጎስ የፖሊስን ጭካኔ የሚመረምር የሕግ ባለሙያዎችን ያካተተ ቡድን ዛሬ ስራ መጀመሩን አስመልክተው ሰላም እንደሚሰፍን ጥሪ አቀረቡ።
ሰልፈኞቹ ከጠየቋቸው ነገሮች መካከል አንዱ በሌጎስ ስለተፈፀመው ግድያ ምርመራ የሚያደርግ ገለልተኛ ቡድን እንዲቋቋም እና ጥፋተኛ ሆነው የተገኙ የፖሊስ አባላት ተጠያቂ እንዲሆኑ ነበር።
ሰልፈኞቹ አክለውም በፖሊስ የተለያዩ በደሎች የደረሰባቸው ግለሰቦች ወይንም ቤተሰቦቻቸው መንግሥት ካሳ እንዲከፍላቸው ጠይቀዋል።
ናይጄሪያ ከሚገኙ 36 ግዛቶች ሌጎስ ገለልተኛ አጣሪ ቡድን በመሰየም ሰዎች ያላቸውን ቅሬታ እንዲያስገቡ ስትጠይቅ የመጀመሪያዋ ከተማ ናት።
ፕሬዝዳንት ቡሃሪ ለአጣሪ ቡድኑ ሙሉ ድጋፍ እንደሚሰጡ ተናግረዋል።
የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት በሌጎስ ሌኪ፣ ስለደረሰው የፖሊስ ጭካኔ የተመላበት እርምጃ ሁሉም መረጃዎች ተጠናቅረው እስኪቀርቡ ድረስ ምንም ዓይነት ጉዳይ ላይ አስተያየት ከመስጠት እንደሚቆጠቡ አስታውቋል።
"ፕሬዝዳንቱ ሰላም፣ ወንድማማችነት፣ እና በማህበረሰቡ መካከል ያለ መተሳሰብ እንዲቀጥል ይጠይቃሉ" ያለው ጽህፈት ቤታቸው፤ እነዚህን የናይጄሪያውያን እሴቶች "አንዳቸው ከሌላኛቸው ጋር በጥላቻ እንዳይተያዩ" በመግለጫው ጥሪ አቅርቧል።
ናይጄሪያውያን ወጣቶች በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች ተቃውሞ መካሄድ ከጀመሩ ከሁለት ሳምንት በኋላ የሚደርሱ ጥፋቶችን የሚመረምር ቡድን ተቋቁሟል።
ፕሬዝዳንት ቡሃሪ አመጽ በተቀላቀለበት ሕዝባዊ ተቃውሞ የተነሳ 69 ሰዎች መሞታቸውን ገልፀው፤ 51ዱ ንፁኀን ዜጎች ናቸው ብለዋል።
የፖሊስ ጭካኔን በመቃወም በናይጄሪያ የተቃውሞ ሰልፍ እያካሄዱ የሚገኙት የ#EndSARS ዘመቻ አንቀሳቃሾች፤የዘመቻውን መሪዎችና አማካሪዎች ለመምረጥ እንቅስቃሴ ጀምረዋል።
ምርጫ ሊደረግ መሆኑን የገለፀው አንድ ማንነቱ ያልተገለፀ ቡድን ሲሆን፤ በበይነ መረብ በሚሞላ ቅጽ በኩል ምርጫ እንደሚካሄድ ተገልጿል።
ይህ በጉግል ላይ ምርጫ የሚካሄድበትን ቅጽ ናይጄሪያውያን በዋትስአፕ እየተቀባበሉት ሲሆን፤ የግዛታቸውን፣ የፌደራል መሪዎችንና አማካሪዎችን እንዲመርጡ ቅስቀሳ እየተደረገ መሆኑን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን ዘግበዋል።
ቅፁ ታዋቂ ሰዎችን፣ ጠበቆችን እንዲሁም የፖለቲካ ተንታኞችን ይዟል።
ቅዳሜ እና እሁድ በናይጄሪያ የተለያዩ ከተሞች ዝርፊያዎች መፈፀማቸው የተገለፀ ሲሆን፤ ፖሊስንም ይህንኑ ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ናይጄሪያውያንን በቁጥጥር ስር አውሏል።
እነዚህ ግለሰቦች በተለያዩ ችሎቶች ዛሬ ቀርበው ክስ ይመሰረታል ተብሎ ይጠበቃል።












