ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ናይጄሪያ፡ 10 አመት የተፈረደበት ታዳጊን እስር ልጋራ ያሉት ፖላንዳዊ
በናይጄሪያዋ ግዛት ካኖ "ሃይማኖቱን አንቋሽሿል" በሚል የአስር አመት እስር የተፈረደበት ታዳጊን "እኔ ልታሰርለት" በማለት በፖላንድ የሚገኝ የኦሽዊትዝ ማስታወሻ ማዕከልና ሙዝየም ዳይሬክተር ለናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ጥሪ አቅርበዋል።
ዶክተር ፒዮትር ሲይዊንስኪ ብቻቸውን ሳይሆን በአለም አቀፍ ያሉ 119 በጎ ፈቃደኞችም በታዳጊው ፈንታ አንዳንድ ወር በሱ ፈንታ እንደሚታሰሩለት ተናግረዋል።
ዶክተሩ ለናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ሙሃማዱ ቡሃሪ "ታዳጊውን ይቅርታ ያድርጉለትና በሱ ፈንታ እኛ እንታሰርም" በማለትም ደብዳቤ ፅፈዋል።
"ምንም ይበል ምን ህፃን እንደመሆኑ መጠን ኃላፊነት እንዳለው ጎልማሳ ሰው ሊቆጠር አይገባም። የተፈረደበት እስርም ህፃንነቱን፣ ወጣትነቱን የወደፊት ተስፋውን የሚነጥቅ ነው። ለማይሽር አካላዊና ስነ ልቦናዊ ጉዳትም ይዳረጋል" በማለት ያሰፈሩ ሲሆን አክለውም
"ነገር ግን ታዳጊው ግዴታ አስር አመት (120 ወራት) በእስር ማሳለፍ አለበት ከተባለ፣ እርስዎም ይህንን ውሳኔ መቀልበስ ካልቻሉ፤ በታዳጊው ፈንታ እኔን ጨምሮ 120 በጎ ፈቃደኞች በሱ ፈንታ አንዳንድ ወር በእስር ለማሳለደፍ ፈቃደኛ ነን" በማለትም በደብዳቤያቸው ተማፅነዋል።
ታዳጊው ከጓደኛው ጋር ሲያደርገው በነበረ ክርክር "ሃይማኖቱንና አምላኩን የሚያዋርድና የሚያንቋሽሽ" ንግግር ተናግሯል በሚልም ወንጀል ነው የካኖ ግዛት የሻሪያ ፍርድ ቤት ውሳኔውን ያሳለፈው።
የታዳጊው ጠበቃ በበኩሉ በህገ መንግሥቱ ላይ የሰፈረውን የህፃናትን መብት ጥሷል በሚልም የተከራከረ ሲሆን ይግባኝም ጠይቋል። ለይግባኙም ፍርድ ቤቱ የሰጠው ተለዋጭ ቀጠሮ የለም ተብሏል።
በናይጄሪያ ውስጥ ካሉ ግዛቶች መካከል ካኖን ጨምሮ አስራ ሁለቱ ከአገሪቱ ህገ መንግሥት በተጨማሪ የሸሪያ ህጎችንም ተግባራዊ ያደርጋሉ።
የተባበሩት መንግሥታት የህፃናት መርጃ ድርጅት፣ ዩኒሴፍ በበኩሉ የፍርድ ቤቱ ውሳኔን እንዲገመግሙት ለባለስልጣናቱ ጥሪ ማድረጋቸው ተዘግቧል።
የኦሽዊትዝ ሙዝየም እንዲህ አይነት ጥሪ ማድረጉ ያልተለመደ የተባለ ሲሆን የናይጄሪያው ፕሬዚዳንትም በዚህ ጉዳይ ላይ ምላሽ አልሰጡም።
በፖላንድ የሚገኘው የኦሽዊትዝ ማስታወሻ ማዕከልና ሙዝየም የቀድሞ የናዚ ማጎሪያ ካምፕ ሲሆን 1.1 ሚሊዮን ይሁዳውያንም በአሰቃቂ ሁኔታ የተጨፈጨፉበት ነው።