ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ስፔንን ከአምባገነን ወደ ዲሞክራሲ ያሻገሩት የቀድሞው ንጉሥ አገር ለቀቁ
ስፔን ትልቅ ተወዳጅነት የነበራቸው ንጉሥ ዥዋን ካርሎስ አገሪቱን ለቀው ወዳልታወቀ ስፍራ ሄደዋል፡፡
አገር እንዲለቁ ያደረጋቸው በቅርቡ ስማቸው ከሙስና ጋር ተያይዞ መነሳቱ ነው ተብሏል፡፡
ንጉሥ ካርሎስ 82 ዓመታቸው ሲሆን አገር ስለመልቀቃቸው ያሳወቁት ለቀድሞው አልጋ ወራሻቸው፣ ለአሁኑ ንጉሥና ልጃቸው ለፍሊፕ ካርሎስ ሳድሳዊ በጻፉት ደብዳቤ ነው፡፡
የቀድሞው ንጉሥ መንበራቸውን ለልጃቸው ያስተላለፉት የዛሬ ስድስት ዓመት ገደማ ነበር፡፡
‹‹ልጄ ሆይ! አቃቢ ሕግ ለምርመራ ከፈለገኝ እመጣለሁ›› ይላል የደብዳቤው ማሳረጊያ፡፡
በንጉሡ ላይ ምርመራ የተከፈተው ባለፈው ሰኔ ወር ሲሆን የሙስና ቅሌታቸው ከሳኡዲ አረቢያ በመካ- መዲና የፈጣን ባቡር ግንባታ ጋር የተሳሰረ ነው፡፡
‹አትፈልጉኝ ደህና ሁኑ›› ያሉት ንጉሥ ወደየት አገር እንደሄዱ ለጊዜው የታወቀ ነገር የለም፡፡
ንጉሥ ካርሎስ ስፔንን ከአምባገነኑ የጄኔራል ፍራንኮ አገዛዝ ወደ ዲሞክራሲ ያሸጋገሩ ብልህ መሪ እንደነበሩ ይነገርላቸዋል፡፡
የቢቢሲው የአውሮጳ ዘጋቢ ኒክ ቢከር እንደጻፈው ለኒህ የተከበሩ ንጉሥ በሙስና ቅሌት መጨረሻቸው ይህ መሆኑ አሳፋሪም አሳዛኝም ነው፡፡
ንጉሥ ካርሎስ ከጎርጎሳውያኑ 1975 ጀምሮ ለአርባ ዓመታት ስፔንን በንግሥና ከመሩ በኋላ በ2014 ነበር ወንበሩን ለልጃቸው ያስተላልፉት፡፡
አሁን ስፔንን የሚያስተዳድራት ንጉሥ ፊሊፕ ሳድሳዊ ሲሆን ለአባቱ ይከፈል የነበረውን የ228ሺ ዶላር ዓመታዊ የኪስ ገንዘብም እንዲቋረጥ አድርጓል፡፡
የቀድሞው ንጉሥ ካርሎስ የተከሰሱበት የፈጣን ባቡር ሥራ ተቋራጭ በሳኡዲ አረቢያ ከመካ ወደ መዲና የሚወስድ የባቡር ሀዲድ ሲሆን 6 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ወጥቶበታል፡፡ ከዚህ ውስጥ የተወሰነውን ወደ ኪሳቸው ሳይዶሉት አልቀሩም፡፡
ይህ በንጉሡ ላይ የተከፈተው የሙስና ምርመራ ስዊዝ ባንክንም ይጨምራል፡፡ የስዊዝ መንግሥት ንጉሡ ላይ ምርመራ ከፍቶባቸዋል፡፡