በስዊድን የ12 አመት ታዳጊ በተባራሪ ጥይት መገደሏ ቁጣን ቀሰቀሰ

ታትሟል

በስዊድን የ12 አመት ታዳጊ በተባራሪ ጥይት መገደሏ ቁጣን የቀሰቀሰ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ አገሪቷ የተደራጁ ቡድኖች የሚፈፅሟቸውን ወንጀሎች የምትፈታበት መንገድ ላይ ክርክሮችና ትችቶች አስከትሏል።

ስሟ ያልተጠቀሰው ታዳጊ ነዳጅ ማደያ አካባቢ ጥይት ሲተኮስ ተባራሪ እንዳገኛትና ህይወቷ እንዳለፈ የአገሪቷ ሚዲያ ዘግቧል።

ጥቃቱ የተፈፀመው በደቡባዊ ስቶክሆልም ሲሆን ፖሊስ የደረሰው እሁድ ጥዋት ላይ ነው።

ምንም እንኳን የተኩስ ልውውጡ ለምን እንደተከሰተ ዝርዝር ይፋዊ መረጃ ባይሰጥም የአገሪቷ ሚዲያዎች እንደዘገቡት አንድ ታጣቂ ሁለት የሌላ ቡድን አባላትን ተኩሶ ለመግደል በተኮሰበት ወቅት ተባራሪ ታዳጊዋን አግኝቷል ተብሏል።

በርካቶች በታዳጊዋ ሞት ሃዘናቸውን እየገለፁ ሲሆን በሞተችበት አካባቢም አበባ በማስቀመጥና ሻማ በማብራት በአጭር የተቀጨ ህይወቷን ዘክረዋታል። በርካቶች በተደራጁ ቡድኖችም ጠንከር ያለ እርምጃ መንግሥት እንዲወስድ እየጠየቁ ነው።

"ይህ ሁኔታ መቼም ቢሆን ሊከሰት አይገባም። የ12 አመት ታዳጊ እኮ ናት የተቀጨችው" በማለት አንድ ግለሰብ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዜና ወኪል ተናግራለች።

ፖሊስ ምርመራ ቢጀምርም እስካሁንም ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር አልዋለም።

የአገሪቷ ባለስልጣናት በቡድን የተደራጁ ወንጀለኞችን ለማስቆም ቃል ቢገቡም በቅርብ አመታት የነዚህ ወንጀሎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀበ ነው።

የፍትህ ሚኒስትሩ ሞርጋን ጆሃንሰን በበኩላቸው በታዳጊዋ ሞት የተሰማቸውን ሃዘንና ቁጭት ገልፀው፤ ከዚህ በኋላ በርካታ ፖሊሶችን እንደሚያሰማሩና ጥቃት ያደረሱትም ላይ ጠበቅ ያለ እስር እንደሚጠብቃቸው ቃላቸውን ሰጥተዋል።

የአገሪቷ ፖሊስ ኃላፊ አንደርስ ቶርንበርግም በተመሳሳይ መልኩ እነዚህን ጥቃቶችን ለመከላከል መንግሥት የበለጠ እርምጃ እንደሚወስድ ቢገልፁም የተቃዋሚ ፓርላማ አባሉ ጆሃን ፎርሴል በበኩላቸው ስዊድን ደህንነቷ የተጠበቀ ለማድረግ ሁኔታዎችን እንደገና ማጤን ያስፈልጋል ብለዋል።

በባለፈው አመት በአገሪቷ ውስጥ እየጨመረ ያለውን የተደራጀ ወንጀል ለመቆጣጠር ልዩ ግብረ ኃይል እንደሚያቋቁሙ ባለስልጣናቱ አስታውቀዋል።

ፖሊስ አደንዛዥ ዕፅና ህገ ወጥ መሳሪያዎች ጋር በተያያዘ በበለጠ ክትትል ለማድረግ የሚያስችል አዳዲስ መመሪያዎች ፀድቀዋል።

በባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ 163 ተኩሶች በተደራጁ ቡድኖች የተከሰቱ ሲሆን 20 ሰዎች መሞታቸውንም ከፖሊስ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

በባለፈው አመትም 334 የተኩስ ልውውጦች ተከስተው 42 ግለሰቦች ሞተዋል።