ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ የሰራው የኮቪድ-19 ክትባት ኬንያ ውስጥ ሊሞከር ነው
የኬንያው የምርምር ተቋም፣ የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ የሰራውን የኮቪድ-19 ክትባትን በውቅያኖስ ዳርቻ ከተማዋ ኪሊፊ ሊሞክር ነው።
ኬምሪ ዌልካም ትረስት የተሰኘው ይህ ተቋም 400 የጤና ባለሙያዎችን ለጥናቱ በበጎ ፈቃደኝነት ይፈልጋል።
የዚህ ጥናት ዓለማ " አንድ ክትባት ለሁሉም" የሚል መሆኑን ተገልጿል።
በመላው ዓለም ተመራማሪዎች የኮቪድ-19 ክትባት ለማግኘት የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን እያከናወኑ ነው። የኦክስፎርዱ ዩኒቨርስቲ "ChAdOx1 nCoV-19" የተሰኘ ክትባት ሰርቶ ከዩናይትድ ኪንግደም ለተውጣጡ ከአንድ ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞች ላይ ሙከራ አድርጓል።
አሁን ደግሞ የኬንያው የሕክምና ምርምር ተቋም የክትባቱን መገኘት ለመደገፍ አብሮ እየሰራ ነው።
አራት መቶዎቹ በጎ ፈቃደኞች እድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ መሆን ያለባቸው ሲሆን በኪሊፊ የጤና ባለሙያ ሆነው እየሰሩ የሚገኙ መሆን እንዳለባቸውም ተገልጿል።
የኮሮናቫይረስ እስካሁን ድረስ ፈዋሽ መድሃኒት ወይም ክትባት ባይገኝለትም ነገር ግን ክትባት መገኘቱ የቫይረሱ ስርጭትን ለመግታትም ሆነ ሕሙማንን ለማከም ወሳኝ ሚና እንዳለው የዓለም ጤና ድርጅት ይናገራል።
አክሎም የሰዎችን በሽታ የመከላከል አቅም በማለማመድ ሻይረሱን በመዋጋት እንዳይታመሙ ያደርጋል ይላል።
በአፍሪካ ውስጥ እስካሁን ድረስ የክትባቱ ሙከራ እየተካሄደ ያለው በደቡብ አፍሪካ ሲሆን ኬንያዊያንም ሙከራውን ለማድረግ እየተጠባበቁ ነበር።
ነገር ግን አሁንም ቢሆን የክትባት ሙከራ ጉዳይ አፍሪካውያንን እያከራከረ ነው። በክርክሩ ገበታ ከፊት የሚሰየመው ደግሞ በነዚህ ሙከራዎች ጀርባ "የቅኝት ግዛት አስተሳሰብ" መንፀባረቁ ነው የሚሉ በርካቶች ናቸው።