ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ የእንግሊዝ ፖሊሶች የሚደርስባቸው የምራቅ መትፋት ጥቃት መጨመሩ 'አስጨንቆናል' አሉ
በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ማግስት በእንግሊዝ ፖሊሶችና ቁልፍ ሰራተኞች ላይ የሚደረገው የምራቅ መትፋት ወንጀል አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደደረሰ ተገለፀ።
ከዩኬ ብሔራዊ ፖሊስ በተሰበሰበ መረጃ መሰረት ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በዚህ ወር ብቻ 14 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ተነግሯል።
የምራቅ መትፋት ጥቃት ለመጨመሩም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ሆኗል እየተባለ ነው።
የኮሮና ወረርሽኝ መዛመትን ለመግታት አስገዳጅ የቤት መቀመጥ መመሪያ ባስተላለፈችው ዩናይትድ ኪንግደም ላይ የተሰማሩ ፖሊሶች ምራቅ የመትፋት ጥቃት እንዳስጨነቃቸው እየተናገሩም ነው።
ምራቅ የሚተፉት ጥቃት አድራሾችም ወደ ፍርድ ሊቀርቡ እንደሚገባ በፍትህ ዘርፍ የተሰማሩ አካላት ጥያቄያቸውን እያቀረቡ ነው።
በእንግሊዝና ዌልስ በተደረገ ጥናት በፖሊሶች ላይ ምራቅ የሚተፉት ጥቃት አድራሾች "በኮሮናቫይረስ ተይዘናል" በማለት እያስፈራሩም እንደሆነ ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል።
በሚያዝያ ወር ብቻ 300 ግለሰቦች በፖሊሶችና በቁልፍ ሰራተኞች ላይ ምራቅ በመትፋት ወንጀል በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን፤ አብዛኛዎቹም ክስ ተመስርቶባቸዋል።
በኖቲንግሃም ሻየር ፖሊስ የሆነው አንቶኒ ብሪስና የስራ አጋሩ በእንጨት ማምረቻ ቦታ አንድ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ሲያውሉ፣ ተጠርጣሪው ምራቅ ተፍቶባቸዋል።
አንቶኒ የኮሮናቫይረስ ምርመራ አድርጎ ነፃ ቢባልም፤ከምርመራው በፊት ግን እሱም ሆነ አጠቃላይ ቤተሰቡ ምን ያህል ተሸብሮ እንደነበር አልደበቀም።
እንዲህ አይነት ተደጋጋሚ ጥቃቶች መድረሳቸው በወረርሽኙ ወቅት የሚሰሩ በርካታ የፖሊስ አባላትን በጣም እንዳስጨነቃቸው ተናግሯል።
"ከህሊናችን የማይጠፋ ጉዳይ ሆኗል። በተለይም መመሪያዎችን ጥሰው በርካታ ሰዎች በሚገኙበት ወቅት ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጭ ይሆናሉ" ብሏል።
በሃገሪቷ አጠቃላይ ምራቅ የመትፋት ጥቃት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ብዙም እንዳላስደነቀው የሚናገረው ፖሊሱ አብዛኛው ህዝብ በአስገዳጅ የቤት መቀመጥ መመሪያ "ተስፋ በመቁረጥ ነው"ም ይላል።
"ሰዎች ሲታዘዙም ሆነ እንዲህ አድርጉ ሲባሉ ደስ አይላቸውም" ብሏል።
በእንጨት ማምረቻ ውስጥ የተፋበት የ32 አመቱ ዳንኤል በጥቃቱ የስድስት ወር እስራት ተፈርዶበታል።
አንቶኒ ግለሰቡ ላይ ክስ ተመስርቶበት ለእስር መብቃቱ አስደንቆታል። ምክንያቱም ከዚህ ቀደም ምራቅ ተተፍቶበት ምንም አይነት እርምጃ እንዳልተወሰደበት ያስታውሳል።
በእንግሊዝ የሚገኙ የተለያዩ የፖሊስ ቢሮዎች በፖሊስ አባላት እንዲሁም ቁልፍ በሚባሉ ሰራተኞች ላይ በዚህ ወረርሸኝ ወቅት የደረሰባቸውን ጥቃቶች አሰባስቧል።
- የቴምስ ቫሊ ፖሊስ እንዳሳወቀው በመጋቢትና ሚያዝያ ወር ውስጥ በፖሊስ አባላት ላይ 198 ያህል ጥቃቶች የደረሱ ሲሆን፤ ከነዚህም መካከል ምራቅ መትፋት፣ ማስነጠስ እንዲሁም መነከስ ይገኝበታል።
- በኬንት በመጋቢትና ሚያዝያ ወር ውስጥ 196 ያህል ወንጀሎች በፖሊሶች የተፈፀሙ ሲሆን፤ ምራቅ የመትፋቱም ሁኔታ ከባለፈው አመት ጋር ሲነፃፀር በእጥፍ ጨምሯል።
- በክሊቭላንድም እንዲሁ በመጋቢትና ሚያዝያ ወር 81 ጥቃቶች በፖሊስ አባላት ላይ ደርሷል።
- የኖቲንግሃም ሻየር ፖሊስ እንዳሳወቀው በመጋቢትና ሚያዝያ 61 የቁልፍ ሰራተኞች ላይ ምራቅ የተተፋባቸው ሲሆን በያዝነውም ግንቦት ወር እንዲሁ 28 ጥቃቶች ተመዝግበዋል።
- በአቮንናና ሶመርሴትም ስድስት የፖሊስ አባላት መነከስ እንዲሁም የኮሮናቫይረስ አለብን ባሉ ሰዎች ላይ ፊታቸው ላይ ምራቅ ተተፍቶባቸዋል።
አብዛኛዎቹም የምራቅ መትፋት ጥቃቶች ሲገመገሙ የኮሮናቫይረስን እናዛምትባችኋለን በሚሉ ማስፈራሪያዎችም የተሞሉ ናቸው ተብሏል።
ጥቃቱን በርካታ የፖሊስ ኃላፈዎችም አውግዘውታል።
በታሜስ ቫሊ ፖሊስ ቢሮ ዋና ኃላፊ የሆኑት ጆን ካምፔል እንደተናገሩት "በፖሊስ አባላትም ሆነ በአደገኛ ሰራተኞች ላይ ምራቅ መትፋት፣ መንከስ በማንኛውም ወቅት አፀያፊ ተግባር ነው። በአሁኑ ሰዓት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት በሆነበት ወቅት ደግሞ የወረደና በቃላትም መግለፅ የሚከብድ ነው" ብለውታል።
ኃላፊው አክለውም ጥቃት የሚደርስባቸውም ሆነ ማንኛውም የፖሊስ አባላት የኮሮናቫይረስ መመርመሪያ እንዳላቸውና ጥቃቱም የደረሰባቸው ሰራተኞች የማህበራዊ ዋስትና ድጋፍ እንዳላቸው ገልፀዋል።
በክሊቭላንድ ቢሮ ፖሊስ ምክትል ኃላፊ ስቲቭ ግራሃም በበኩላቸው "በርካታ ጥቃቶች መደረሳቸው የፖሊስ አባላቱን ሞራል በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዳው ነው" ብለዋል።
"ልክ እንደ ማንኛውም የማህበረሰብ አባል በኮሮናቫይረስ የሚደርስባውን ጫና ተቋቁመው እየሰሩ ባሉበት ወቅት እንዲህ አይነት ጥቃቶች ተቀባይነት የላቸውም። ለደህንነታቸውም ልናስብ ይገባል ብለዋል"
ሌሎች ኃላፊዎችም ጥቃቱ የሚያደርሱት ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃ እንዲወሰድባቸውም ጥሪ አቅርበዋል።