ኮሮናቫይረስ፡ በምዕራብ ሐረርጌ ጉባ ኮሪቻ በኮቪድ-19 የተያዘው ግለሰብ ማን ነው?

አፉን የሸፈነ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ረቡዕ ዕለት ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው አራት ግለሰቦች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ገልጾ ሦስቱ ከፑንትላንድ መምጣታቸውን፤ አንዱ በምዕራብ ሐረርጌ ጉባ ኮሪቻ ነዋሪ የሆነ ግለሰብ ግን ቫይረሱ ካለበት ሰው ጋር ንክኪም ሆነ የጉዞ ታሪክ እንደሌለው በመግለጽ ቫይረሱ እንደተገኘበት ካስታወቀ በኋላ ጉዳዩ እየተጣራ ነው ተብሎ ነበር።

በምዕራብ ሐረርጌ በጉባ ኮሪቻ በኮቪድ-19 እንደተያዘ የተነገረው ወጣት፣ ካሊፍ ጃሚር [ስሙ የተቀየረ] እንዴት በቫይረሱ ሊያዝ ቻለ በማለት ተኝቶ ወደሚታከብት ሂርና ሆስፒታል በመደወል አነጋግረነዋል።

በአሁኑ ሰዓት በሂርና ሆስፒታል ለይቶ ማከሚያ ውስጥ የሚገኘ ካሊፍ፤ በሆስፒታሉ ውስጥ ከእርሱ ውጪ ሌላ የኮቪድ-19 ታማሚ እንደሌለ ለቢቢሲ ገልጾ የጤና ባለሙያዎችም አስፈላጊውን እንክብካቤ በሙሉ እያደረጉለት መሆኑን ይናገራል።

አሁን ስላበት ጤንነት ሁኔታ ሲጠየቅም "ይህ በሽታ እንዴት እንደያዘኝ አላውቅም፤ ምንም የሚያመኝ ነገር ስለሌ ተይዣለሁ ብዬም አላስብም" ብሏል።

በምዕራብ ሐረርጌ ነዋሪ የሆነው ካሊፍ ጤና ሚኒስቴር የጉዞ ታሪክ የለውም ይበል እንጂ እርሱ ግን በጅቡቲ በኩል ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለመሄድ ሲሞክር ጅቡቲ ላይ በቁጥጥር ስር ውሎ ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለሰ ነግሮናል።

"ጅቡቲ ደሂል የምትባል ቦታ 11 ቀን ነው የቆየነው። ከዚያ ፖሊስ [የጅቡቲ] ይዞን ወደ ኢትዮጵያ መለሰን" ካለ በኋላ፣ እርሱና ጓደኞቹ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ ለ12 ቀናት በድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ለይቶ ማቆያ ውስጥ መቀመጣቸውን ለቢቢሲ አስረድቷል።

የ Facebook ይዘትን ይለፉት

የሚፈልጉት ይዘት የለም

በ Facebook ተጨማሪ ይመልከቱቢቢሲ ከሌሎች ድረ-ገጾች ለሚመጡ መረጃዎች ሀላፊነት አይወስድም.

የ Facebook ይዘት መጨረሻ

የ14 ቀን የለይቶ ማቆያ ቆይታ በኋላ ወደ ጭሮ ከዚያም ቤተሰቦቹ ወዳሉበት ስፍራ እንዳቀና እና እዚያም ለ14 ቀናት እንደቆየ ነግሮናል።

የካሊፍ እድሜ በጤና ሚኒስቴር መግለጫ ላይ 23 እንደሆነ ቢገለጽም እርሱ ግን "19 እንኳ አልሞላኝም" ብሏል።

"ድሬዳዋ እንዳለን አትጨባበጡ፣ የምግብ እቃዎችን በጋራ አትጠቀሙ፤ ከቤተሰቦቻችሁ ጋር አትቀላቀሉ ተብሎ ምክር ተሰጥቶን ነበር በዚህም ምክንያት ከቤተሰቦቼ ጋር አልተቀላቀልኩም፤ ሰላምም ያልኳቸው በሩቁ ነው" ይላል።

ነገር ግን በቫይረሱ መያዙ ከተረጋገጠ በኋላ ቤተሰቦቹን ጨምሮ ከእርሱ ጋር ንክኪ አላቸው ተባለው የተጠረጠሩ ከ70 በላይ ሰዎች ተለይተው ክትትል እየተደረገላቸው ነው።

እንዴት የኮቪድ-19 ምርመራ እንደተደረገለት የተጠየቀው ካሊፍ፣ በጉባ ኮሪቻ 12 ቀናት ከቆየ በኋላ ከእርሱ ጋር አብሮ የነበረ ጓደኛው ስለታመመ ወደ ጭሮ እንዲመጣ በጤና ጽህፈት ቤት ሰዎች እንደተደወለለትና እንደተመለሰ ይናገራል።

ጭሮ ከደረሰ በኋላ ናሙና ተወስዶ ሲመረመር ቫይረሱ እንዳለበት እንደተነገረው ገልጿል።

በምዕረራብ ሐረርጌ የኮቪድ-19 ህክምና ማዕከል ሆኖ እያገለገለ የሚገኘው የሂርና ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር አሊይ አደም፤ ወጣቱ በጥሩ ሁኔታ እንዳለ ገልፀው ከእርሱ ጋር ንክኪ ያላቸው ተብለው የተጠረጠሩ 75 ሰዎች ተለይተው ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑንም አመልክተዋል።

"ምንም ህመም የለውም፤ የኮቪድ-19 ምልክቶች የሉትም፤ አልፎ አልፎ ሳል ብቻ ይታይበታል" ሲሉ ገልፀዋል።

የሂርና ሆስፒታል የኮቪድ 19 ህክምና ማዕከል ሆኖ እየተደራጀ ሲሆን 100 አልጋዎችና ሁለት መካኒካል ቬንትሌተሮች አሉት።

ሆስፒታሉ በአጠቃላይ 110 ሠራተኞች ሲኖሩት 67 የጤና ባለሙያዎች፣ 43 ደግሞ ተጨማሪ ህክምና ድጋፍ የሚሰጡ ናቸው።

ሆስፒታሉ በአንዴ እስከ 100 ሰው ማስተናገድ ሚችል ቢሆንም ያሉት ግን 60 አልጋዎች ናቸው።

ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ ለ18 ሺህ 754 ሰዎች ምርመራ ያደረገች ሲሆን 66 ሰዎች ከወረርሽኙ አገግመዋል።

ኮሮና