ኮሮናቫይረስ፡ 300ሺህ አፍሪካውያን በኮቪድ-19 ምክንያት ሕይወታቸውን ሊያጡ ይችላሉ-የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ያለበቂ መከላከያ 300ሺህ አፍሪካውያን በኮሮና ምክንያት ህይወታቸውን እንደሚያጡ ይገመታል ሲል ዛሬ ባወጣው መግለጫ ላይ አስታወቀ።
የኮሮና ቫይረስ በአፍሪካውያን ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት በገመመገመበት በዚህ መግለጫ ከሰው ህይወት በተጨማሪ የአህጉሪቷን ምጣኔ ኃብት እያሽመደመደው እንደሆነም አስፍሯል።
በዚህ አመት የአህጉሪቱ ምጣኔ ሃብት በ3.2 በመቶ ያድጋል ተብሎ የተገመተ ቢሆንም ቫይረሱ ባደረሰው ጫና ምክንያት ምናልባት 1.8 በመቶ ሊያድግ ይችላል ብሏል።
ይህም ሁኔታ 27 ሚሊዮን ህዝብን ለረሃብ እንደሚያጋልጥ የኮሚሽኑ መግለጫ ጠቁሟል።
ኮሚሽኑ ነገ ይፋ በሚያደርገው ሪፖርት ቫይረሱ ካስተለው ቀውስ ጋር ተያይዞም ደካማ የሚባለው የአህጉሪቷጤና ስርዓት ለተጨማሪ ወጪ እንደሚዳረግም አስገንዝቧል።
እስካሁን ባለው መረጃ በአህጉሪቷ ውስጥ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 16 ሺ ሲሆን 800 ሰዎችም ህይወታቸውን አጥተዋል፤ ይህ ቁጥር እየጨመረ ሊሄድ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ የአህጉሪቱ የጤና ስርአትም ጥያቄ ውስጥ እንደሚገባ መግለጫው አመላክቷል።
ይህንንም ለመታደግ የመንግሥታት ቁርጠኝነት እንዲሁም ድጋፍ እንደሚገባም የኮሚሽኑ ዋና ፀሐፊ ቬራ ሶንግዌ ገልፀዋል።
" የአህጉሪቱን የጋራ ብልጽግና ለመከላከልና ለመንባት፤ መንግሥታት ለዜጎቻቸው በአስቸኳይ መሰረታዊ ፍላጎታቸውን ማቅረብ እንዲችሉ 100 ቢሊየን ዶላር ያስፈልጋል" ብለዋል
" የወረርሽኙ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ቫይረሱ በቀጥታ ከሚያደርሰው ጉዳት የበለጠ ነው" ያሉት ፀሐፊዋ በአፍሪካ አገራት በአጠቃላይ ምጣኔ ሃብታቸው ቫይረሱ እንደተከሰተ መጎዳት መጀመሩን ገልጠዋል።
"ወረርሽኙን ለመከላከል ተብሎ የተቀመጠው አካላዊ ርቀትን መጠበቅ የኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን እግር ተወርች አስሯል" ሲሉ አስረድተዋል
የኮሚሽኑ ሪፖርት አክሎም አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ድጋፍ ካልተደረገላቸው በስተቀር ሙሉ በሙሉ እንደሚዘጉ አትቷል።
የአፍሪካን ምጣኔ ሃብት 40 በመቶ የሚሸፍነው ዘይት በግማሽ ዋጋው መቀነሱን፣ በዋነኝነት አፍሪካ ወደውጪ የምትልካቸው የጨርቃ ጨርቅና አበባ ምርቶችም መውደቃቸውን ጠቅሷል።
ቱሪዝም የአንዳንድ የአፍሪካ አገራት አጠቃላይ ብሔራዊ ምርትን 38 በመቶ ቢይዝም አየር መንገዶች ስራቸውን በማቋረጣቸው ምክንያት ሙሉ በሙሉ ቆሟል ሲል ያትታል።
የአፍሪካ ምጣኔ ሃብት የተሳሰረ ነው ያለው ሪፖርቱ ለቀውሱም የምንሰጠው ምላሽ " ወደ አንድ ሊያመጣን ይገባል" ብሏል።













