በመላው ኢትዮጵያ ያጋጠመው የኤሌክትሪክ መቋረጥ ምክንያቱ ምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ትናንት ከአመሻሽ ጀምሮ በመላው አገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ ሥርዓት ላይ ባጋጠመ ችግር ምክንያት የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ተቋርጦ ነበር።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር እቶ ሞገስ መኮንንም የኃይል መቋረጥ ማጋጠሙን ትናንት ምሽት ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
ነገር ግን ላጋጠመው የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ ምክንያቱ ምን እንደሆነ አለመታወቁን ገልጸው፣ ነገር ግን ከግልገል ጊቤ ሦስት ከሚቀርበው የኃይል አቅርቦት መስመር ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችልና ተቋማቸው የችግሩን ምንጭ ለማወቅና መፍትሄ ለመስጠት እየሰራ መሆኑን አቶ ሞገስ ተናግረው ነበር።
ከሰዓታት በኋላም በግልገል ጊቤ ማመንጫዎች ቦታ የጣና በለስና የፊንጫ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን ከኃይል አቅርቦት ሥርዓቱ ጋር በማገናኘት የዋና ከተማዋ አዲስ አበባ የተወሰኑ አካባቢዎች ኃይል እንዲያገኙ መደረጉም ታውቋል።
ግን ምንድን ነው ያጋጠመው?
አቶ ሞገስ ዛሬ ቅዳሜ ጠዋት ለቢቢሲ እንደገለጹት ላጋጠመው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ምክንያት የሆነው በግልገል ጊቤ ሁለት የኃይል ማመንጫ አካባቢ በጣለ ከባድ ዝናብ ሳቢያ መሆኑን አመልክተዋል።
የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ ጨምረውም ከባዱ ዝናብ በግልገል ጊቤ ሁለት ላይ ባስከተለው ችግር ምክንያት የኃይል ማመንጫው ተግባሩን በአግባቡ ማከናወን ባለመቻሉ የመቆጣጠሪያ ሥርዓቱ በእራሱ አሰራር ኃይል የማግኛ መስመሩን ወደ ግልገል ጊቤ ሦስት በማሸጋገር አገልግሎቱን ለመቀጠል ተሞክሯል።
ይህ ደግሞ በግልገል ጊቤ ሦስት የኃይል ማመንጫ ላይ ያልተጠበቀ ክፍተኛ ጫና በማስከተሉ ግልገል ጊቤ ሦስትም ሥራውን በአግባቡ እንዳያከናውን ምክንያት ሆኖ አገልግሎት በማቆሙ በአገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ለሰዓታት እንዲቋረጥ ምክንያት መሆኑን አቶ ሞገስ እብራርተዋል።
አክለውም የድርጅታቸው ባለሙያዎች ችግሩን ለመቅረፍ የኃይል መቋረጡ ካጋጠመበት ጊዜ ጀምሮ ጥረት እያደረጉ መሆኑን አመልክተው ሙከራ እየተደረገባቸው ካሉ አንዳንድ እካባቢዎች በስተቀር በሁሉም ቦታዎች ላይ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት መመለሱን ተናግረዋል።













