በየመን የአልቃኢዳ መሪ በአሜሪካ የአየር ጥቃት ተገደለ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በአረብ ልሳነ ምድር የአልቃኢዳ መሪ ነው የታባለውን ግለሰብ አሜሪካ መግደሏን ገለጸች።
ከአምስት ዓማት በፊት ጀምሮ ጂሃዳዊ ቡድኑን ሲመራ ነበር የተባለው ቃሲም አል-ራይሚ የአሜሪካ ኃይሎች የመን ውስጥ በፈጸሙት ወታደራዊ ተልዕኮ መገደሉን የአሜሪካ መንግሥት አስታውቋል።
የተገደለው የጂሃዳዊው ቡድኑ መሪ በአውሮፓዊያኑ በ2000ዎቹ ውስጥ በምዕራባዊያን ጥቅሞች ላይ ከተፈጸሙ ተከታታይ ጥቃቶች ጋር ግንኙነት እንዳለው ሲነገር ቆይቷል።
ቃሲም አል-ራይሚ የመሪነት ቦታው የያዘው ቀድሞ ቡድኑን ሲመራ የነበረው ግለሰብ አሜሪካ በሰው አልባ አውሮፕላን በፈጸመችበት ጥቃት ከተገደለ በኋላ ነበር።
በአረብ ልሳነ ምድር የአልቃኢዳ ክንፍ የተባለው ይህ ቡድን የመሰረተው ከ10 ዓመት በፊት በሳኡዲ አረቢያና የመን ከነበሩ የአልቃኢዳ ቡድኖች ተወጣጥቶ ነበር።
ዓላማውም በመካከለኛው የአረቡ ዓለም ያሉና በአሜሪካ የሚደገፉ መንግሥታትን ከስልጣን መገልበጥና በአካባቢው ያለውን የምዕራባዊያንን ተጽዕኖ ሙሉ ለሙሉ ማስወገድ ነው።
ቡድኑ በፈጸማቸው አብዛኞቹ ድርጊቶች የተሳካለት ለዓመታት ባለመረጋጋት ውስጥ በቆየችው የመን ውስጥ እንደሆነ ይነገራል።
የቃሲም አል-ራይሚ በአሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላን የመገደል ወሬ መናፈስ ጀምሮ የነበረው ከሳምንት በፊት የነበረ ሲሆን፤ ይህንን ለማስተባበል የሚመራው ቡድን ከመገደሉ ቀደም ብሎ የተቀረጸ ነው የተባለ የድምጽ መልዕክት አሰራጭቶ ነበር።
አሁን ግን ከዋሽንግተን ይፋ የተደረገው መግለጫ የአል-ራይሚ ሞትን ያረጋገጠ ቢሆንም መቼ እንደተገደለ ግን ያለው ነገር የለም።
"የእሱ ሞት በአካባቢውና በዓለም ዙሪያ ያለውን የአልቃኢዳ እንቅስቃሴን በማዳከም ቡድኑ በብሔራዊ ደህንነታችን ላይ የጋረጠውን ስጋት ለማስወገድ ከምንችልበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ያስችለናል" ብሏል የአሜሪካ መንግሥት ባወጣው መግለጫ።
አክሎም "በአል-ራይሚ ሞት አሜሪካ፣ ጥቅሞቻችንና አጋሮቻችን ደህንነታቸው ከስጋት ነጻ ይሆናል" ሲል የግለሰቡ ሞት ያለውን ፋይዳ አመልክቷል።












