ኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የመኪና ሽያጭን ማቃወሱ ተነገረ

ታትሟል

በኮሮናቫይረስ ምክንያት በየካቲት ወር የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ ቻይና ውስጥ የመኪኖች ሽያጭ በ92 በመቶ መቀነሱን የዘርፉን ንግድ የሚከታተለው አካል አሳወቀ።

የገዳዩን ቫይረስ መስፋፋት ለመቆጣጠር ሲባል የሰዎች እንቅስቃሴ በመገደቡ ገዢዎች ወደ መኪና ነጋዴዎች መሄድ በማቆማቸው ሽያጩ በከፍተኛ ደረጃ እንዲያሽቆለቁል ምክንያት ሆኗል።

በመላው ቻይና በየካቲት ወር የመጀመሪያ ሳምንት ላይ በቀን በአማካይ 811 መኪኖች ብቻ በመሸጣቸው ግብይቱ በ96 በመቶ ቀንሷል።

የቻይና መኪና አምራቾች ማህበር እንደሚለው የመኪና ሽያጭ ተቋማት በሮቻቸውን ሲከፍቱ ሽያጩ እየጨመረ እንደሚሄድ ተስፋውን ገልጿል።

"በየካቲት ወር መጀመሪያ ሳምንት ላይ ብዙ ሰዎች ከቤታቸው ስላልወጡ ወደ መኪና መሸጫ መደብሮች አንድም ሰው ብቅ አላለም ነበር" ብለዋል የማህበሩ ዋና ጸሐፊ ቹይ ዶንግሹ።

ከቻይና መኪና አምራቾች መካከል አንዱ የሆነው ጂሊ በገዢና በሻጭ መካከል ያለውን ንክኪ ለማስቀረት በኢንትርኔት በኩል የሚከናወን ሽያጭን አዘጋጅቷል። በዚህም ገዢዎች ትዕዛዛቸውን በኢንተርኔት በኩል አቅርበው መኪናቸው ቤታቸው ድረስ እንዲመጣ ይደረጋል።

ስታቲስታ የተባለው የመረጃ ምንጭ እንደሚለው ባለፈው የፈረንጆች ዓመት 21 ሚሊዮን መኪኖችን በመሸጥ ቻይና በምድራችን ላይ ከፍተኛው የመኪና ሽያጭ የተከናወነባት አገር ናት። አሜሪካ ደግሞ በሁለተኛ ደረጃ ትከተላታለች።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከመከሰቱ ቀደም ብሎ በኢኮኖሚ መቀዛቀዝና ከአሜሪካ ጋር በነበረ የንግድ ውዝግብ በቻይና ውስጥ የነበረው የመኪኖች ሽያጭ እየቀነሰ ነበር።

በርካታ የመኪና አምራች ኩባንያዎች በዚህ ሳምንት ሥራቸውን ለመጀመር አስበው ነበር። ነገር ግን ቀደም ብለው ሥራ የጀመሩት ድርጅቶች የምርት ሥራቸውን እንዳሰቡት እያካሄዱ አይደለም። በሙሉ አቅማቸው ለማምረትም ረጅም ጊዜ ሊጠይቃቸው እንደሚችልም አመልክተዋል።

በኮሮናቫይረስ ምክንያት በምርት ሥራቸው ላይ መስተጓጎል ያጋጠማቸው የመኪና አምራች ድርጅቶች ብቻ ሳይሆኑ "የዓለማችን ፋብሪካ" በምትባለው ቻይና የሚገኙ ሌሎችም ችግሩ ገጥሟቸዋል።

በርካቶችም የምርት መዘግየት እንደሚያጋጥም ገልጸው አፕልም በቅርቡ የአይፎን ስልኮች አቅርቦት እጥረት በዓለም ዙሪያ ሊያጋጥም እንደሚችል አስጠንቅቋል።