ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዛሬ 6 ሺህ ዓመት የታኘከው ማስቲካ የያዘው ምስጢር ይፋ ሆነ
ይህ የዛሬ 6 ሺህ ዓመት በስካንዲናቪያ የኖረች ሴት መልክ ነው። መልኳን ማወቅ የተቻለው አኝካ በተፋችው ማስቲካ ላይ በተደረገ ምርምር ነው። ተመራማሪዎቹ ማስቲካው ላይ ካረፈው የጥርሷ አሻራ የዘረ መል ምርመራ አድርገዋል። ከዚያም ማን ነበረች? የሚለውን መተንተን ችለዋል።
ተመራማሪዎቹ እንዳሉት ከሆነ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰራ የምርምር ዓይነት ነው። ከዚህ ቀደም ስለ ጥንታዊ ሰው ለማወቅ ከአጥንት ላይ በሚወሰዱ መረጃዎች ነበር ምርምሩ የሚሰራው።
የዛሬ ስድስት ሺህ ዓመት በስካንዴኔቪያ የኖረችው ሴት ጠየም ያለ ቆዳ፣ ጥቁር ቡናማ ጸጉር እንዲሁም ሰማያዊ አይን ነበራት ተብሏል።
ከዩኒቨርስቲ ኦፍ ኮፐንሀገን የመጡት ዶ/ር ሐንስ ሽሮይደር "ማስቲካው" ከዛፍ ላይ የተወሰደ ሙጫ ነገር ነው። ጥንታዊ ዘረ መልን ለማወቅ ወሳኝ ግብዓት ሆኖ አገልግሏል። በተለይ ደግሞ የሰው ልጅ ቅሪት በሌለን የጊዜ ሰሌዳ ውስጥ ሲሉ ስራቸውን ያስረዳሉ።
"የጥንታዊ ሰው የተሟላ ዘረ መል ከአጥንት ውጪ ማግኘት የሚገርም ነው" ብለዋል።
የጥንታዊቷ ሴት ሙሉ ጄኔቲክ ኮድ [ጂኖሜ] ምን እንደምትመስል ለማወቅ ለማስቻል ሲባል ተሰርቷል።
መልኳ በአብዛኛው በወቅቱ በአውሮጳ፣ እንዲሁም መካከለኛው ስካንዴኔቪያ ውስጥ የኖሩት አዳኝና ፍራፍሬ ለቃሚ የነበሩ ሰዎችን ይመስላል። ጠይም፣ ጥቁር ቡናማ ጸጉር እና ሰማያዊ አይኖች አሏት።
ዘረ መሉ የተገኘው በወቅቱ የድንጋይ መሳሪያዎችን ለማጣበቅ የሚያገለግል ጥቁር ቡናማ ቀላጭ ነገር መታኘኩን የሚያሳይ የጥርስ ምልክት በመገኘቱ ነው። ይህ ቀላጭ ነገር የታኘከው ይበልጥ እንዲያጣብቅ ታስቦ ካልሆነም የጥርስ ሕመምን ለማስታገስ ይሆናል የሚሉ መላምቶች ተቀምጠዋል።
በዴንማርክ የድንጋይ ዘመን ቅሪተ አካሎች በሚገኙበት ስፍራ የተገኘው ይህ የታኘከ ማስቲካ፣ ፍንጭ የሰጣቸው ተመራማሪዎች ምርምራቸውን በዘረ መል ፍተሻው ላይ አደረጉ።
ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት በዚህ በታኘከ ማስቲካ ላይ ያለው መረጃ የዘመኑ ሰው እንዴት እንደኖረ፣ የጤናው ሁኔታ ለማወቅ የሚያስችል መረጃ ይዟል።
ከዚህ የታኘከ ማስቲካ ላይ የተወሰደ የዘረ መል የሰው ልጅ በሂደት እያጠቁት የመጡት የበሽታ ዓይነቶች እንዴት ራሳቸውነ እየለወጡ እንደመጡም ለማወቅ መረጃ ይዟል ብለዋል።
ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት በጥንት ዘመን የሳንባ ምች [ኒሞኒያ] እንዲከሰት የሚያደርገውን እንዲሁም ሌሎች ቫይረሶችና ባክቴሪያዎችን ከዚህ የታኘከ ማስቲካ ውስጥ ፈልቅቀው ማውጣት፣ ማጥናትና በሽታ አምጪ ሕዋሳት በዘመናት መካከል ምን ያህል እንደተለወጡ ማወቅ ይችላሉ።