የሳኡዲው ዜጋ በአሜሪካ፣ ፍሎሪዳ ሦስት ሰዎችን ገደለ

ፔንስኮላ የባህር ኃይል መንደር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

አንድ የሳኡዲ የአቪየሽን ተማሪ አሜሪካ፣ ፍሎሪዳ በሚገኘው ፔንሰኮላ የባሕር ኃይል ማሰልጠኛ ውስጥ ባደረሰው ጥቃት ሦስት ሰዎችን ገድሎ በርካቶችን አቆሰለ።

ከድርጊቱ በኋላ ከሳኡዲው ንጉሥ ሰልማን የስልክ ጥሪ ደረሰኝ ያሉት ዶናልድ ትራምፕ "ንጉሡ ድርጊቱን አረመኒያዊ ሲሉ ኮንነውታል" ብለዋል።

ትራምፕ በትዊተር ሰሌዳቸው እንደጻፉት ንጉሥ ሰልማን ለአሜሪካ ሕዝብና ለተጎጂ ቤተሰቦች በጥቃቱ ከልብ ማዘኔን ንገርልኝ ብለዋቸዋል።

ጥቃት አድራሹ ሦስቱን ሰዎች የገደላቸው ሽጉጥ ተኩሶ ነው። ቢያንስ 8 ሰዎችንም አቁስሏል። ኋላ ላይ ፖሊስ ጥቃት አድራሹን ተኩሶ ገድሎታል።

የፍሎሪዳ አገረ ገዢ የሆኑት ሮን ዴሳንቶስ ሳኡዲ ለተጎጂዎች ካሳ ትሰጣለች ብለዋል።

ጥቃት አድራሹ ሞሐመድ ሳኢድ አልሻርማኒ እንደሚባልና በፔንስኮላ የአቪየሽን ተማሪ እንደነበረ ከመገለጹ ውጭ ተጨማሪ መረጃዎች አልወጡም።

የአሜሪካ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ጥቃት አድራሹ ለዚህ ድርጊት ያነሳሳው ምን እንደሆነ ገና ምርመራ እያደረገ እንደሆነ የገለጸ ሲሆን ድርጊቱ ከሽብርተኞች ጋር ተያያዥ ስለመሆኑ ያለው ነገር የለም።

"በርካታ መላምቶች ሊሰነዘሩ ይችላሉ። እኛ ግን እውነትን ማፈላለግ ነው ሥራችን ብለዋል" ልዩ የወንጀል ምርመራ ቡድን መኮንን ራቼል ሮጃስ።

ንጉሥ ሰልማን በድርጊቱ የሳኡዲ ሕዝብ እጅግ መቆጣቱን ጠቅሰው የግለሰቡ ድርጊት የሳኡዲን ሕዝብ አይወክልም ብለዋል። ንጉሡ "የሳኡዲ ሕዝብ አሜሪካንን ይወዳል" እንዳልዋቸው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጽፈዋል።

ትራምፕ የሳኡዲ የሰብአዊ መብት ጥሰት እምብዛምም ሳያሳስባቸው ከአገሪቱ ጋር እጅና ጓንት ሆነው የሚሠሩ መሪ ናቸው።

በተለይም ሳኡዲ በኦክቶበር 2018 በቱርክ ኢስታንቡል እጅግ በሚዘገንን ሁኔታ እንደተገደለ በተገለጸው የሳኡዲ አረቢያ ዜጋና የዋሺንግተን ፖስት ጋዜጠኛ ጃማል ኻሾግጂ እጇ አለበት የሚሉ ሪፖርቶች ከወጡ ወዲህ ትራምፕ ሳኡዲን እንዲያገሉ በአገሪቱ እንደራሴዎች ጭምር ቢጠየቁም አሻፈረኝ ብለዋል።

ካርታ

ሳኡዲ አረቢያ እጅግ አስፈላጊ ሸሪካችን ናት ሲሉ ልኡል ቢን ሳልማን ቀጥተኛ ትእዛዝ ሰጥተውበታል ተብሎ የሚገመተውን የኻሾግጂን አሰቃቂ ግድያ ገሸሽ አድርገውታል።

ጥቃት አድራሹ መሐመድ ሰኢድ አልሻመራኒ በሳኡዲ አየር ኃይል ተለማማጅ ሊውተናንት ሲሆን ጥቃቱን ከመፈጸሙ በፊት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ አላማውን ጽፎ ነበር የሚሉ መረጃዎች ወጥተዋል።

በዚህ የባሕር ኃይል መንደር ድርጊቱን ተከትሎ በርካታ የሳኡዲ ሰልጣኞች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ኒውዮርክ ታይምስ ጽፏል።

እንደ አሜሪካ ባሕር ኃይል መግለጫ ከሆነ 20 የሚሆኑ የሳኡዲ ወታደሮች በዚህ ፔንሰኮላ የአየር ኃይል መንደር ውስጥ ስልጠና ላይ ነበሩ።

የቀድሞው የፍሎሪዳ አገረ ገዢ ሪክ ስኮት ለጋዜጠኞች "አሜሪካኖች በገዛ አገራቸው የሚገደሉበት ሁኔታ ማብቃት አለበት፣ እኛን ለሚጠሉ ሰዎች እኛው የወታደራዊ ስልጠና የምንሰጥበት ሁኔታም ማብቃት አለበት" ብለዋል።

የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ማርክ ኢስፐር በበኩላቸው ወደ አሜሪካ የሚመጡ ሰዎች ማንነት ላይ ጥብቅ ፍተሻ ሊደረግ ይገባል ብለዋል።