በናይጄሪያ 'ደደቦች' የሚል ስያሜ የነበረው ሰፈር ስም ተቀየረ

የናይጄሪያው ደደቦች ሰፈር ስም ሲሻር
ታትሟል

በሰሜናዊ ናይጄሪያ 'ደደቦች' የሚል ስያሜ የነበረው አንድ መንደር ኗሪዎች ለዘመናት ባሰሙት ቅሬታ ስሙ እንዲቀየር ተደረገ።

'ደደቦች' የሚለው የሃውሳ ቋንቋ ቃል 'Unguwar Wawaye' የመንደሩ ስያሜ ተሽሮ ሰፈሩ 'የብዙ ነገሮች መገኛ' መባሉን ይፋ ያደረጉት የአካባቢው ኢማም ናቸው።

የአካባቢው ሰዎች ከ 'ደደቦች' ሰፈር ነው የመጣነው በማለታቸው ለዓመታት መቀለጃ ሲሆኑ ስለኖሩ ከየት እንደሆኑ እንኳ መናገር እንደሚከብዳቸው ሲገልፁ ቆይተዋል።

ባላ ሳኒ የተባለ የአካባቢው ኗሪ "ለሰዎች የመጣሁት 'ከደደቦች' ሰፈር ነው ብሎ መናገር በጣም የሚያሳፍር ነገር ነው። አሁን ግን በኩራት የመጣሁት 'ከብዙ ነገሮች መገኛ' ነው እላለው" በማለት ለቢቢሲ ገልጿል።

የአካባቢው ኗሪ እዚያ መንደር ተገኝተው አሳፋሪው የሰፈሩ ስም ተሽሮ አዲስ ስም መሰጠቱን ያበሰሩትን ኢማም አመስግነዋል።

መንደሩ 'ደደቦች' ሰፈር የሚለውን መጠሪያ ያገኘው ከ70 ዓመታት በፊት ሰዎች አካባቢው ላይ ከሚገኘው 'ደደብ' ወንዝ አቅራቢያ መስፈራቸውን ተከትሎ እንደሆነ ይነገራል።

ወንዙ ራሱ ግን ለምን እንደዛ ተብሎ እንደተጠራ ለብዙዎች ግልፅ አይደለም።