እሥር ቤት ሆኖ ባጭበረበረው ገንዘብ ቤትና መኪና የገዛው ናይጄሪያዊ ተደርሶበታል

የፎቶው ባለመብት, EFCC
በይነ-መረብን [ኢንተርኔት] ተጠቅሞ በማጭበርበሩ ለእሥር የተዳረገው ናይጄሪያዊ ማረሚያ ቤት ሆኖ አንድ ሚሊዮን ዶላር መዝብሯል ተብሎ ምርመራ እየተደረገበት ነው።
የናይጄሪያ ፀረ-ሙስና ሰዎች ሆፕ ኦሊሴጉን አሮኬ አጋሮቹን ተጠቅሞ ነው ሲያጭበርብር የነበረው ይላሉ።
ሆፕ፤ ከሰባት ዓመት በፊት በማጭበርበር ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ የ24 ዓመት እሥር ተፈርዶበት ከፍተኛ ጥበቃ በሚድረግበት እሥር ቤት ይገኛል።
ግለሰቡ ሌጎስ ከሚገኘው እሥር ቤት ታዛው ውስጥ የበይነ-መረብ አገልግሎት አግኝቶ አሁንም ሰዎችን ሲያጭበርብር ነበር ይላል የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ሰዎች ያወጡት ሃተታ።
ኮሚሽኑ በለቀቀው ዘገባ፤ ሆፕ ኦሊሴጉን ከሌሎች እሥረኞች በተለየ የኢንተርኔት አገልግሎት ያገኛል፤ ስልኩን እንደልቡ ይጠቀምም ነበር። አልፎም በሕመም ምክንያት ሆስፒታል ሄዶ ተኝቷል ቢባልም እሱ ግን ሆቴል እያደረ ሚስትና ልጆቹን እንዳሻው ሲያገኛቸው ነበር ተብሏል። ሠርግና ልደት ሁሉ ይታደም እንደነበር ደርሼበታለሁ ይላል የኮሚሽኑ ዘገባ።
ሃሰተኛ ስም ተጠቅሞ ሁለት የባንክ ሂሳቦች የከፈተው ሆፕ በጣም ውድ መኪናና ልጥጥ ቤት ገዝቷል። አልፎም የሚስቱን የባንክ ሂሳብ ያጭበረበረውን ገንዘብ ለማዘዋወር እንደተጠቀመበት ደርሼበታለሁ ሲል ኮሚሽኑ ይፋ አድርጓል።
የኮሚሽኑ ሰዎች ግለሰቡ ለምን ወደ ሆስፒታል እንደሄደ፤ እንዴትስ አድርጎ ሆቴል ማረፍ እንደቻለና በነፃነት ሲዘዋወር እንደበር እያጣርን ነው ብለዋል።
ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግበት የኪሪኪሪ ማረሚያ ቤት ሰዎች በጉዳይ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ዜናው ናይጄሪያውያንን እጅጉን ያስደነገጠ ነው ይላል የቢቢሲው የናይሪያ ወኪል ንዱካ ኦሪጂንሞ። እንዴት ሆኖ ነው ተፈርደቦት ዘብጥያ የወረደ ወንጀለኛ በነፃነት ሠርግና እና ልደት የሚታደመው? ሲሉ ይጠይቃሉ።
ብዙዎች ግለሰቡ ለማረሚያ ቤቱ ሰዎች ጠርቀም ያለ ጉርሻ ሳይሰጥ እንዳልቀረ ይገምታሉ። ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ተጠያቂው መንግሥት ነው ባይ ናቸው። ምክንያቱም የማረሚያ ቤቱ ባለሥልጣናት የሚከፈላቸው ገንዘብ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።












