በኬሚስትሪ የተግባር ፈተና ምክንያት ተማሪዎችና መምህራን ታመሙ

ታትሟል

በኬንያ ኪሱሙ በአንድ ትምህርት ቤት ቤተ ሙከራ ውስጥ ነው ነገሩ የተፈጠረው።

ተማሪዎቹና መምህራኑ የታመሙት በቤተ ሙከራ ውስጥ በተማሪዎቹ የተግባር ፈተና ላይ በተፈጠረ የአደገኛ ጋዝ ትነት ምክንያት ነው ተብሏል።

ከታመሙ መምህራን መካከል ነፍሰጡር የነበረችው አንዷ በእርግዝናዋ ላይ እክል አጋጥሟታል ተብሏል።

ችግሩ የተፈጠረው ተማሪዎቹ ለተግባር ፈተናቸው ሳይክሎሄክሳን የተሰኘ ውህድ መጠቀም ሲኖርባቸው ዛይለን የተሰኘውን በመጠቀማቸው ነው ተብሏል።

ይህ የሆነው ደግሞ ሳይክሎሄክሳን ኬንያ ውስጥ ገበያ ላይ ስለሌለ በምትኩ ተማሪዎች ዛይለንን ይጠቀሙ የሚል ትእዛዝ ከኬንያ የብሄራዊ ፈተናዎች ኤጀንሲ ለትምህርት ቤቱ በመተላለፉ እንደሆነ ተገልጿል።

የዛይለን ተንን(እንፋሎትን) በትንሹ እንኳ መሳብ እራስ ምታትና መዛል ዓይነት ህመሞችን ያስከትላል። እስከ ሞትም ሊያደርስ የሚችልባቸው አጋጣሚዎች አሉ።

ተማሪዎች ዛይለንን እንዲጠቀሙ ያዘዙት የፈተናዎች ድርጅት ሃላፊዎች ስለ ኬሚካሉ አደገኝነት ይወቁ አይወቁ የታወቀ ነገር የለም።

ቢሆንም ግን የኪሲሙው ትምህርት ቤት መምህራን ለተፈጠረው ነገር የኬንያን ፈተናዎች ድርጅትን ተጠያቂ አድርገዋል።