ግብጽ ውስጥ አንድ የኤድስ ህመምተኛ በግድ ከሆስፒታል መውጣቱ ቁጣ ቀሰቀሰ

ታትሟል

ኤችአይቪ በደሙ ውስጥ ያለ ግለሰብ ረቡዕ እለት በግድ ከሆስፒታል እንዲወጣ ሲደረግ የሚያሳይ ምስል ከታየ ኋላ የተቀሰቀሰ ቁጣን ተከትሎ የግብጽ ባለሥልጣናት በጉዳዩ ላይ ምርመራ መጀመራቸው ተገለጸ።

ከዋና ከተማዋ ካይሮ 100 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘውና ጋርቢያ ተብሎ በሚታወቀው የግብጽ ሰሜናዊ ክልል ውስጥ ባለ ካፍር ኤል ዛያት በተባለ ሆስፒታል ውስጥ ህመምተኛው መሬት ላይ በኃይል እየተጎተተ እንዲወጣ ሲደረግ የሚያሳየው ቪዲዮ በርካታ ሰዎችን አስቆጥቷል።

በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት የተሰራጨውን ቪዲዮን ተከትሎ የመንግሥት ባለሥልጣናት አስፈላጊውን ምርመራ እንደሚያደርጉ አሳውቀዋል።

የግብጽ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፤ ድርጊቱን የፈጸሙት የሆስፒታሉ ሠራተኞች ለህመምተኛው ተገቢ አገልግሎት ባለመስጠት ተጠያቂ እንደሚደረጉም አሳውቋል።

ስማቸው ያልተጠቀሰ አንድ የሆስፒታሉ ከፍተኛ ኃላፊ እንዳሉት ግን የኤድስ ህመምተኛ የሆነው ግለሰብ ወደ ሆስፒታሉ ሲመጣ አደንዛዥ ዕፅ ተጠቅሞ እንደነበር ተናግረዋል።

ስለክስተቱ በስፋት ከተነገረ በኋላ የአገሪቱ ብሔራዊ ኤችአይቪ/ኤድስ ፕሮግራም ኃላፊዎች ወደ ሆስፒታሉ ሄደው ህመምተኛውን ለማግኘት ቢሞክሩም ሊያገኙት አልቻሉም።

ኃላፊዎቹ ከሆስፒታሉ በግድ እንዲወጣ የተደረገውን ግለሰብ በማግኘት ለኤድስ ህሙማን ብቻ ህክምና ወደሚደረግበት ሆስፒታል እንዲገባና አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያገኝ ጥረት እያደረጉ ነው።

በግብጽ ውስጥ የሚገኙ የኤችአይቪ ኤድስ ህሙማን ከፍተኛ የሆነ መገለል እንደሚደርስባቸው ይነገራል።