በናይጄሪያ የታገደው እስላማዊ ቡድን መሪ ለሕክምና ወደ ህንድ እንዲሄዱ ተፈቀደ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የናይጄሪያ ፍርድ ቤት በሀገሪቱ የታገደውንና የኢራን መንግሥት ደጋፊ ናቸው ተብለው የሚከሰሱት ሺያ ሙስሊሞችን መሪ ከሶስት ዓመት እስር በኋላ ለሕክምና ወደ ሕንድ እንዲሄዱ ፈቀደ።
የኢብራሂም ዛክዛኪ ደጋፊዎች በዋና ከተማዋ አደባባዮቹ ላይ ወጥተው መሪያቸው እንዲለቀቁ ሲጠይቁ ነበር።
ሼኹ ዛክዛኪ የ66 ዓመት አዛውንት ሲሆኑ በከባድ የሰው ነፍስ ማጥፋት ወንጀልና ሌሎች ጥፋቶች ተከስሰው ዘብጥያ ቢወርዱም እርሳቸው ግን የቀረበባቸውን ክስ ሁሉ አስተባብለዋል።
የሼኹ ደጋፊዎቹ እንዳሉት መሪያቸው ቀላል ስትሮኮች እንዳጋጠማቸውና አንደኛው የዓይናቸውን ብርሀን ማጣታቸውን ይናገራሉ።
ፍርድ ቤቱ ሼኽ ዛክዛኪን ከሕክምና በኋላ ተመልሰው የፍርድ ሂደታቸውን እንዲከታተሉ በሚል ወደ ሕንድ ሲያቀኑ አጅበዋቸው የሚሄዱ ሰዎች እንዲኖሩ አዟል።
እስላማዊ ንቅናቄው በናይጄሪያ በሼኽ ዛክዛኪ ከአራት አስርታት በፊት የተመሰረተ ሲሆን "በአምባገነንነትና በጨቋኝነት ላይ በእውነትና በፍትህ የተገኘ ድል" ሲል የፍርድ ቤቱን ውሳኔ አድንቋል።
የንቅናቄው አባላት የናይጄሪያ ባለስልጣናትን ከ2015 ጀምሮ በእስር ላይ ያሉት ሼኽ ዛክዛኪና ባለቤታቸው ማላማ ዜናት ኢብራሂም ላይ ጉዳት በማድረስ ይወነጅላሉ።
ቡድኑ በናይጄሪያ ውስጥ የታገደው በጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር 2015 ሐምሌ ወር ለተከታታይ ሳምንታት የተቃውሞ ሰልፍ ካካሄደ እና በዚህም የተነሳ ሰልፈኞቹ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ተጋጭተው ከፍተኛ የፖሊስ ሹምን ጨምሮ 350 ሰዎች ከሞቱ በኋላ ነው።
በወቅቱ የጸጥታ ኃይሎቹ እርምጃውን የወሰዱት ኃላፊያቸውንና አጃቢዎቻቸውን ለመከላከል መሆኑን ተገልጾ ነበር።
ሼክ ዛክዛኪ በ2015 በቁጥጥር ስር ከዋሉ በርካታ የቡድኑ ደጋፊዎች መካከል አንዱ ናቸው።
የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት የሆኑት ሙሐመዱ ቡሀሪ ቡድኑ " በሰላማዊ ተቃውሞ በማያምኑ ጽንፈኞች ተውጧል" ሲሉ ተናግረው ነበር።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ፖሊስ በሰልፈኞች ላይ የወሰደውን እርምጃ ኮንነዋል።
የንቅናቄው ደጋፊዎች የናይጄሪያ መንግሥትን እውቅና የማይሰጡ ሲሆን ሼኽ ዛክዛኪ ብቻ በሀገሪቱ ሙሉ ስልጣን ያላቸው መሪ አድርገው ይቀበላሉ።
ንቅናቄው በሚሰባሰብበት ወቅት ለአያቶላህ ኮሀሜይኒ ያለውን ታማንነት ስለሚገልጥ ተቺዎች ከኢራን ጋር ጥብቅ ቁርኝት አላቸው ሲሉ ይተቻሉ።
ንቅናቄው በሰሜናዊ ናይጄሪያ ሆስፒታሎችና ትምህርት ቤቶች ያሉት ሲሆን እነዚህን ተቋማት ለማንቀሳቀስ ከኢራን መንግሥት ይደገፋል መባላቸውን አስተባብለዋል።












