ኤር ካናዳ ከካናዳ ወደ ሲድኒ ሲበር በገጠመው መንገጫገጭ ጉዳት ደረሰ

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, ከአደጋው በኋላ የነበረውን ሁኔታ የሚያሳይ በአውሮፕላኑ ተሳፋሪዎች የተቀረፀ
ታትሟል

ኤር ካናዳ ወደ ሲድኒ እያደረገ በነበረው በረራ ላይ በተፈጠረ ከባድ መንገጫገጭ 37 ሰዎች ተጎድተው አውሮፕላኑ በአስቸኳይ ለማረፍ ተገዷል።

አውሮፕላኑ ሠራተኞቹን ጨምሮ 284 ሰዎችን አሳፍሮ የነበረ ሲሆን፤ ከቫንኮቨር ወደ ሲድኒ እያደረገ የነበረውን በረራ አቋርጦ ሀዋኢ ለማረፍ ተገዷል።

ጉዳት የደረሰባቸው ተሳፋሪዎች ወደ ሆኖሉሉ የተወሰዱ ሲሆን፤ ዘጠኙ ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው ባለስልጣናት ተናግረዋል።

ኤር ካናዳ እንዳለው ቦይንግ 777-200 አውሮፕላኑ "ጥርት ባለ ሰማይ ላይ ድንገት የሚከሰት መንገጫገጭ ገጥሞት ነበር" ብሏል።

አዲስ በረራ እስኪመቻች ድረስ ለደንበኞቹ በሆኑሉሉ ሆቴል እንደያዘላቸውም ገልጿል።

"አየር ላይ ተጋጨንና ሁላችንም ከአውሮፕላኑ ጣሪያ ጋር ተላተምን፤ ሁሉም ነገር ወደቀ. . . ሰዎች ከመቀመጫቸው ተነስተው ሲንሳፈፉ አየን" በማለት የተናገረችው ጄስ ስሚዝ የተባለች አውሮፕላኑ ውስጥ የነበረች ተሳፋሪ ናት።

"የመቀመጫ ቀበቷቸውን ያላሰሩ ሰዎች ወደ አውሮፕላኑ ጣሪያ ሲወረወሩና ሁሉም ነገር ሲወድቅ ተመልክተናል፤ ውጥረት የሞላበት ነበር" ብሏል ሌላ ተሳፋሪ።

የድንገተኛ አደጋ ጊዜ ሰራተኞች ተሳፋሪዎችን ሲረዱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

አክሎም "ከፊት ለፊቴ ተቀምጠው የነበሩ ሰዎች ከመቀመጫቸው ተስፈንጥረው ተነስተው የሻንጣ ማስቀመጫው ገጭቷቸው ወደ መቀመጫቸው ሲመለሱ አይቻለሁ" ብሏል።

አውሮፕላኑ ውስጥ የተነሳ ፎቶ፤ አየር መሳብያው ተላቆና የምግብና መጠጥ ማቅረቢያው እዚህም እዚያም ወዳድቆ ይታያል።

ተሳፋሪዎች የአውሮፕላኑ ሠራተኞች ተጎድተው መመልከታቸውን ተናግረዋል።

ጥርት ባለ ሰማይ ላይ የሚፈጠር መንገጫገጭ በሙያ ቋንቋ መጥሪያው ካት (CAT) የሚባል ሲሆን፤ ኩልል ባለ ሰማይ ላይ ምንም አይነት የሚታይ ደመና ሳይኖር የሚፈጠር መንገጫገጭ ነው።

ይህ የሚሆነው ጥርት ባለ ሰማይ ውስጥ በፍጥነት የሚንቀሳቀስ አየር ሲኖር ሲሆን፤ በአይን ለመለየት አዳጋች ነው።

አውሮፕላን አብራሪዎች የሌላ አውሮፕላንን ሪፖርት ከትራፊክ መቆጣጠሪያ ክፍል ወስዶ በመጠቀም የዚህን አየር እንቅስቃሴ ሊከታተሉ ይችላሉ።

የኤር ካናዳ ንብረት የሆነው ቦይንግ 777-200 አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images