በሱዳን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ መክሸፉ ተነገረ

ቃል አቀባዩ ጄነራል ጀማል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

ሱዳንን እያስተዳደረ ያለው ወታደራዊ የሽግግር መንግሥት የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ መክሸፉን ገለጸ።

ቃል አቀባዩ ጄነራል ጀማል ኦማር፤ በሱዳን ብሔራዊ ቴሌቭዥን ጣቢያ ቀርበው እንደተናገሩት፤ በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው የተጠረጠሩ አካላት በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

ከታሰሩት መካከል ጡረታ የወጡ የቀድሞ ወታደራዊ ኃላፊዎች እንዲሁም የአገሪቱ የደህንነት አባላትም ይገኙበታል።

"የአገሪቱን ደህንነት አደጋ ውስጥ የሚጥልና የዜጎችን ፍላጎት ያላገናዘበ ተግባር ያከናወኑ" ሲሉ ሰዎቹን ገልጸዋቸዋል።

የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው በወታደራዊው የሽግግር መንግሥትና ተቃዋሚዎች መካከል ይደረጋል የተባለውን ሥልጣን የመጋራት ስምምነት ለማስቆም ያለመ መሆኑንም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

ስምምነቱ መቼ እንደሚፈረም እስካሁን አልታወቀም።

የአገሪቱ ወታደራዊ የሽግግር መንግሥት እንደሚለው፤ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ሲደረግ ይህ ሦስተኛው ነው።

የሱዳን ጉዳዮች ተንታኝ አህመድ ኮዶዋ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ብዙዎች መግለጫውን ቢጠራጠሩም፤ የሽግግር መንግሥቱን ለማደናቀፍ የሚሞክሩ ኃይሎች መኖሩ እሙን ነው።