ሶማሊያዊው የኡበር ታክሲ ሾፌር ሰዎችን አሰቃይቷል ተባለ

ታትሟል

አሜሪካ፣ ቨርጂንያ ውስጥ ኡበር (የታክሲ አይነት) ይነዳ የነበረ ዩሱፍ አብዲ አሊ የተባለ ግለሰብ ሶማሊያ ሳለ ሰዎችን ማሰቃየቱን ፍርድ ቤት አረጋገጠ።

ዩሱፍ እንደጎርጎራሳውያኑ አቆጣጠር በ1980 በነበረው የሶማሊያ የእርስ በእርስ ጦርነት ወቅት ሰዎችን ማሰቃየቱ ተገልጿል።

ዩሱፍን የከሰሰው ፋራህ ታኒ ዋርፋ የተባለ ግለሰብ ሲሆን፤ ሶማሊያ ሳሉ ኮለኔል የነበረው ዩሱፍ እንዳሰቃየውና እንደተኮሰበትም ለፍርድ ቤት ተናገሯል።

በአገሪቱ ብሔራዊ ጦር ውስጥ ኮማንደር የነበረው ዩሱፍ፤ የአምባገነኑ ሞሀነድ ዚያድ ባሬ ደጋፊ እንደነበር ለፍርድ ቤት የቀረቡ ሰነዶች ያሳያሉ።

ፍርድ ቤቱ ከሠላሳ ዓመት በፊት ፋራህን በማሰቃየት ዩሱፍን ጥፋተኛ ሆኖ ስላገኘው፤ 500,000 ዶላር ካሳ እንዲከፍል ወስኗል።

ፋራህ እንዳለው፤ በ1987 የዩሱፍ ወታደሮቹ ከቤቱ አግተው ወስደውት ነበር። መረጃ ለማግኘት ለወራት እንደተደበደበና እንደተተኮሰበትም ተናገሯል። መቃብሩን እንዲቆፍሩ ለተላኩ ሰዎች ጉቦ በመስጠት ሕይወቱን እንዳተረፈም አክሏል።

ለመጀርያ ጊዜ የዩሱፍ ማንነት ይፋ የተደተገው 1992 ላይ በካናዳ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በተሠራ ዘጋቢ ፊልም ላይ ነበር። ዘጋቢ ፊልሙ ላይ የተካተቱ ምስክሮች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ማሰቃየቱን ተናግረዋል።

ያኔ ቶሮንቶ ውስጥ በጥበቃ ሥራ ይተዳደር የነበረ ሲሆን፤ ካናዳ በሰው መብት ጥሰት አባራው ነበር። ተመሳሳይ እርምጃ በአሜሪካ ቢወሰድበትም በአልታወቀ መንገድ ተመልሶ ወደአሜሪካ ገብቷል።

የሲኤንኤን ዘጋቢዎች የታክሲ ተሳፋሪ በመምሰል ጥያቄዎች አቅርበውለት ነበር። ከሳምንት እስከ ሳምንት ራይድና ሊፍት በተባሉት የታክሲ አገልግሎቶች እየሠራ ገንዘብ ለማግኘት እንደሚሞክር ተናግሮ ነበር።

የኡበር ሹፌር ለመሆን ቀላል እንደሆነ ከመቀጠሩ በፊት ስለማንነቱ ከማጣራት ያለፈ ምንም አለመደረጉን ተናግሯል።

የኡበር ሹፌር ከመቀጠሩ በፊት አሜሪካ ውስጥና ከአሜሪካ ውጪ ወንጀል አለመሥራቱ፤ በኤፍ ቢ አይና በኢንተርፖል አለመፈለጉም ይጣራል።

ዩሱፍ በአሁን ወቅት ከኡበር መተግበሪያ እንደታገደ የኡበር ቃል አቀባይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የሊፍት ቃል አቀባይ "ነገሩ እጅግ አስደንግጦናል" ብለው፤ ሹፌሩ እንዳገዱትን በፖሊስ ምርመራ እንደሚተባበሩ ተናገረዋል።

ዩሱፍ በኡበር ሹፌርነት የሠራው ለ18 ወር ሲሆን፤ ከዛ በፊት ዋሽንግተን ዲሲ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ የጥበቃ ሠራተኛ ነበር።

የፋራህ ጠበቃ ካቲ ሮበርትስ "ከብዙ ጥረት በኋላ የተገኘ ድል ነው" ብለዋል። ፋራህ ለ31 ዓመታት ፍትህ ሲጠብቅ እንደነበርም አክለዋል።

ሶማሊያ ውስጥ በተከናወነ ወንጀል አሜሪካ ውሰጥ የመጠየቅ አሠራር የፍርድ ሂደቱን አጓቶታል።

የአሜሪካ ሕግ አሜሪካ ውስጥም ይሁን ከአሜሪካ ውጪ ስቃይ ለደረሰባቸው ሰዎችን ከለላ ይሰጣል። አሜሪካዊ የሆኑም ያልሆኑም ሰዎች ስቃይ ደርሶብናል ብለው መክሰስ ይችላሉ።