ኢትዮጵያዊቷ የቤት ሠራተኛ በዲፕሎማት አሠሪዋ ጥቃት ደረሰባት

ጾታዊ ጥቃት

የፎቶው ባለመብት, gazzetta

ታትሟል

ከትናንት ወዲያ በአዲስ አበባ፤ የካ ክፍለ ከተማ በሚገኘው ፀሐይ የመኖሪያ አፓርትመንቶች ውስጥ አንድ የውጪ ሀገር ዜግነት ያለው ግለሰብ የቤት ሠራተኛውን ገፍትሮ በመጣል ጉዳት ማድረሱ ተሰማ።

በግቢው ነዋሪ የሆኑት አቶ ዳንኤል በለጠ እንደተናገሩት፤ ሰኞ እለት 10 ሰዓት አካባቢ ቤታቸው ሳሉ ልጆቻቸውን ከትምህርት ቤት ያመጡላቸው ሹፌሮች አፓርትመንቱ ውስጥ አረቦች ከኢትዮጵያዊት የቤት ሰራተኛቸው ጋር ተጣልተው ደረጃ ላይ ገፍትረው እንደጣሏት መስማታቸውን አጫውተውናል።

ነገሩን እንደሰሙ ወደተባለው ሕንፃ መሄዳቸውን የሚያስታውሱት አቶ ዳንኤል፤ አራተኛ ፎቅ ላይ አንዲት ሴት ወድቃ ስትንፈራፈር ማየታቸውን ነግረውናል።

ኋላም የሆነውን ሲጠይቁ፤ አሠሪዋ የሆነ ግለሰብ ገፍትሯት ደረጃው ላይ መውደቋ እንደተገሯቸውና ግለሰቡም ግቢው ውስጥ በሚገኘው አፀድ እንደተቀመጠ እንደሰሙ ያስታውሳሉ።

ጉዳት አደረሰ የተባለው ግለሰብ ተቀምጦ ወደነበረበት በመሄድ ሲያናግሩት፤ እንደገፈተራት ነገር ግን እንዳልጣላት መናገሩን የሚያስታውሱት አቶ ዳንኤል፤ ወደሀኪም ቤት እንዲወስዳት ቢጠየቅም አሻፈረኝ በማለት ለአንድ ሰአት ያህል አምባጓሮ ተፈጥሮ መቆየቱን ነግረውናል።

በኋላም የወደቀችውን ልጅ አፋፍሰው በማንሳት እንዳወረዷት እና ግቢው ውስጥ ሳር ላይ እንዳስተኟት የሚናገሩት አቶ ዳንኤል፤ ግለሰቡ ወደ ቤቱ ገብቶ በመቆለፍ ሊያናግረቸው ፈቃደኛ ሳይሆን መቅረቱን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ ብሩክ፣ ፀሐይ የመኖሪያ አፓርትመንቶች ውስጥ ለሚኖሩ ግለሰቦች በሹፍርና እንደሚሠሩ ተናግረው፤ በዕለቱ መኪናቸው ውስጥ ሳሉ አንዲት ሴት ግቢው ሳር ላይ ተኝታ ስትንፈራፈር ማየታቸውን ያስታውሳሉ።

ጠጋ ብለው ሲመለከቱ አይኗ ስለሚገለባበጥ የከበቧት ሴቶች በሁኔታው ተደናግጠው ይጮሁ እና ያለቅሱ እንደነበርም ነግረውናል።

የግቢው አስተዳደርና ነዋሪዎች ፖሊስ መጥራታቸውን እሳቸውም አረብኛ ስለሚናገሩ ፖሊሶቹን በማስተርጎም ማገዛቸውን ያስታውሳሉ። ጉዳቱን ያደረሰው ግለሰብ ፖሊሶቹንም ሆነ እሳቸውን መገፈታተሩንና ተጎጂዋን ወደ ሆስፒታል ለመውሰድ አሻፈረኝ ማለቱን አቶ ብሩክ ያስታውሳሉ።

አቶ ብሩክም ሆኑ አቶ ዳንኤል እንደሚናገሩት፤ በግቢው የሚኖር ሌላ ሱዳናዊ ወጥቶ በአረብኛ ካነጋገረው በኋላ በእርሱ መኪና ተጎጂዋን ከመኖሪያ አፓርትመንቱ አቅራቢያ ወደሚገኘው ወደ አይሲ ኤም ሲ ሆስፒታል እንደወሰዳት እና በእዚያ ህክምና ክትትል ማግኘቷን ይናገራሉ።

ግጭቱ በተከሰተበት ቤት ፊት ለፊት በቤት ሠራተኝነት የምትሠራና ስሟ እንዲገለጥ ያልፈለገች ሴት ለቢቢሲ እንደተናገረችው፤ ግለሰቡ ከሚስቱና ከሁለት ልጆቹ ጋር አብሮ ይኖራል።

ይህችን ሠራተኛ የቀጠሯት ከ12 ቀን በፊት መሆኑን አስታውሳ፤ ግጭቱ ከመድረሱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ አሠሪዋ ልጅቷ ሥራ እንደማትችል እንደነገረቻት ታስታውሳለች።

ወ/ሮ ቤዛ በግቢው ነዋሪ ሲሆኑ፤ የተፈጠረውን ነገር ከሥራ ከመጡ በኋላ መስማታቸውን ከዚያም በኋላ ግለሰቡ ፖሊሶችን እና ነዋሪዎችን ሲያመነጫጭቅ ማየታቸውን ነግረውናል።

በኋላም ሠራተኛዋ ሕክምና አግኝታ ከመጣች በኋላ እንደገና ራሷን በመሳቷ በድጋሚ ሆስፒታል አፋፍሰው መውሰዳቸውን እና ለሊቱን እዚያው ማሳለፏን ነግረውናል።

ለተጎጂዋ ግለሰብ እህት ደውለን ስለጉዳዩ ለማጣራት ስንጠይቅ፤ አሁን ጉዳዩ በሽምግልና መፈታቱን እንዲሁም ያወጣችውን የሕክምና ወጪ ለመሸፈን በመስማማት ይቅርታ እንደጠየቋት በመናገር ተጨማሪ መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚሰሩና ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉ ግለሰብ እንዲህ አይነት በውጭ ሀገር ዲፕሎማቶች የሚደርሱ ጥፋቶች ሲኖሩ አቤቱታው ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በፅሁፍ መቅረብ እንደሚኖርበት ጠቅሰዋል። ጉዳዩ የሚቀርብለት ክፍል የተፃፈለትን ደብዳቤ መሰረት በማድረግ አቤቱታ ለቀረበበት ኢምባሲ ደብዳቤ እንደሚፅፍ ኢምባሲውም በደሉን አደረሰ ለተባለው ግለሰብ ጉዳዩን እንደሚያቀርብና ሁለቱ ወገኖች የተፈጠረውን ችግር በሽምግልና እንዲፈቱ ለማድረግ ጥረት እንደሚያደርግ ይናገራሉ።

መስሪያ ቤቱ የዜጎች መብትም እንዳይጣስ፣ በመንግሥታት መካከል ያለውም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትም እንዳይበላሽ እንደሚጥር የሚናገሩት ባለሙያው ጉዳዩ የከፋ ከሆነ ግን የሚወሰዱት እርምጃዎችም እንደሚለያዩ ጠቅሰዋል።

ከአዲስ አበባ እንዲሁም ጉዳዩን ከሚከታተለው የካ ፖሊስ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።አቤቱታው ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቀርቦ ከሆነም በሚል ያደረግነው ማጣራት አልተሳካም።