የቤተሰቦቹን መሬት ለማስመለስ ሕግ ያጠናው ኡጋንዳዊ ወጣት

ታትሟል

ኡጋንዳዊው ጆርዳን ኪኒዬራ አባቱ በፍርድ ቤት ክርክር ተረተው መሬታቸውን ሲነጠቁ የስድስት ዓመት ብላቴና ነበር። ይህ ቁጭት ግን በተሸናፊነት እንዲቀመጥ አላደረገውም፤ 18 ዓመት ሙሉ በትምህርት ዓለም ውስጥ ቆይቶ፣ የሕግ ትምህርቱን ተከታትሎ፣ ከ23 ዓመት በኋላ አባቱ የተነጠቁትን መሬት አስመልሷል።

ሰኞ ዕለት ከፍተኛው ፍርድ ቤት የመጨረሻ ያለውን ውሳኔውን ሲሰጥ ቤተሰቦቹ ከ23 ዓመት በፊት ፍትህ ተዛብቶ የተነጠቁትን መሬት መልሰው ማግኘት ችለዋል።

ኪኒዬራ ለቢቢሲ ሲናገር በስድስት ዓመቱ ቤተሰቦቹ መሬታቸውን ሲያጡ ያኔ "ሕይወቴ ተለወጠ" ብሏል።

"ጠበቃ ለመሆን ወሰንኩ፤ ነገር ግን አብዛኛው ለውሳኔዬ የረዳኝ ነገር እያየሁ ያደግኩት ነገር፣ ቤተሰቦቼ ያለፉበት የፍርድ ቤት ውጣ ውረድ፣ ተስፋ መቁረጥና አጋጣሚዎች ናቸው።" ሲልም አክሏል።

ነገሩ እንዲህ ነው እ.ኤ.አ በ1996 አባቱ በጎረቤቶቻቸው የመሬት ይገባኛል ጥያቄ ተነስቶባቸው ፍርድ ቤት ቀረቡ፤ ከዚያም የፍርድ ሂደቱ ለሁለት አስር ዓመታት ዘለቀ።

"አባቴ ጡረታ ወጥቷል፤ ስለዚህ ሕይወቱ ከእጅ ወደ አፍ ነው፤ በጣም ተስፋ ቆርጧል። በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሲሆንና ምንም ማድረግ ሳይችል ሲቀር አንዳች ልብ የሚነካና የሚረብሽ ነገር አለው፤ ያ ነው ይበልጥ ያነሳሳኝ" ይላል ያለፈውን ሲያስታውስ ።

ኪኒዬራ ለቢቢሲ እንዳለው ለአባቱ እርሱ ደስተኛ ነው፤ አባቱ ላለፉት 23 ዓመታት መሬታቸው ጦሙን አድሮ አንዲት ጭራሮ ማቆም ሳይችሉ ኖረው ነበር።

የዘገየ ፍትህ ከተከለከለ ፍትህ ጋር አንድ ነው የሚለው ኪኒዬራ " አባቴ የ82 ዓመት አዛውንት ሲሆን አሁን ማረስ አይችልም፤ ነገር ግን ልጆቹ ከዚህ መቀጠል ይችላሉ" ሲል ተስፋውን ተናግሯል።

በኡጋንዳ የመሬት ክርክር የተለመደ ነው። እንደ የሕግ አማካሪ ቡድኑ ናማቱቲ ከሆነ በሀገሪቱ ግምሽ ያህሉ ባለይዞታዎች የመሬት እሰጥ አገባ ክርክር አለባቸው።

ኪኒዬራ ከቀያቸው ተፈናቅለውና ለረጅም ዓመታት በመጠለያ ጣቢያዎች ኖረው የሚመለሱ በርካታ ኡጋንዳውያን ራሳቸውን የመሬት ክርክር ውስጥ ያገኙታል። እርሱም በሙያው በርካታ ግለሰቦችን እያገዘ ነው።