ናይጄሪያ ውስጥ የከብት ሌቦች 17 ፖሊሶች መግደላቸውና ሌሎች አጫጭር ዜናዎች

ታትሟል

ኢትዮጵያ

• በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በኦሮሚያ ክልል አጎራባች አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት ጠርጥሬያቸዋለው ያላቸውን አምስት የክልሉ አመራሮች በቁጥጥር ስር ማዋሉን የፌደራል ፖሊስ አስታወቀ።

በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል የክልሉ አስተዳደርና ፀጥታ ጉዳዮች ምክትል ሃላፊና የቀድሞ የአሶሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ይገኙበታል።

• በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የሚገኘው የስፔስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሳተላይት መቆጣጠሪያ ጣቢያ አስመረቀ።

ማዕከሉ ከሳተላይት የሚመጡ መረጃዎችን መሰብሰብና ሳተላይቱ ምን አይነት መረጃዎችን መሰብሰብ እንደሚገባው ትእዛዝ የሚተላለፍበት ነው ተብሏል።

ናይጄሪያ

• በሰሜን ምዕራብ ናይጄሪያ ከአካባቢው ገበሬዎች ከብት ለመስረቅ የሞከሩ ታጣቂዎች 17 ፖሊሶችን ገደሉ።

ገበሬዎቹን ለመከላከል የመጡት ፖሊሶች ያልጠበቁት ጥቃት ቢደርስባቸውም፤ በምላሹ 100 ታጣቂዎችን ገድለዋል።

ቦትስዋና

• የቦትስዋና ፓሰርላማ አባላት በዝሆኖች ላይ ህጋዊ አደን እንዲጀመር ፈቀዱ።

ሃገሪቱ 130 ሺ ዝሆኖች ያሏት ሲሆን፤ ቁጥሩ ከአለም አንደኛ ያደርጋታል።

ሱዳን

• የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ኦማር አል በሽር ለሶስተኛ ጊዜ ለመወዳደር ያቀረቡትን ጥያቄ የሃገሪቱ ፓርላማ ተቀበለው።

በፈርነጆቹ 1989 ወደ ስልጣን የመጡት አልበሽር ህገ መንግስቱ ካልተቀየረ ለሶስተኛ ጊዜ መወዳደር አይችሉም።

ኬንያ

• ኬንያዊው የረጅም ርቀት ተወዳዳሪ ኤሉይድ ኪፕቾጌ የዓመቱ ምርጥ ወንድ አትሌት ተብሎ በአለማቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተመረጠ።

ኮሎምቢያዊቷ ካትሪን ኢባርጉዌን ደግሞ የዓመቱ ምርጥ ሴት አትሌት መሆን ችላለች።

ሶማሊያ

• አሜሪካ ከሶማሊያ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከሰላሳ ዓመታት በኋላ እንደገና ጀመረች።

ከዚህ ቀደም ተቀማጭነቱን በኬንያ ናይሮቢ ያደረገው ኤምባሲ አሁን በሞቃዲሾ በሚከፈተው ኤምባሲ ዶናልድ ያማማቶ አምባሳደር እንደሚሆኑ ታውቋል።

ብራዚል

• ብራዚል ውስጥ በሕይወት ከሌለች እናት በተለገሰ ማሕፀን የመጀመሪያዋ ህፃን ተወለደች።

በሕይወት ካለ ሰው በተለገሰ ማህጸን 11 ሕጻናት ቢወለዱም፤ በሕይወት ከሌለች እናት በተለገሰ የማህፀን ህጻን ሲወለድ ግን የመጀመሪያው ነው ተብሏል።

ህንድ

• ህንድ የኢንተርኔት አገልግሎቴን ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግርልኛል ያለችውን ሮኬት ወደ ህዋ አመጠቀች።

ሮኬቱ 5845 ኪሎግራም የሚመዝን ሲሆን፤ እጅግ የተራቀቀ ቴክኖሎጂ ተገጥሞለታል ተብሏል።

አሜሪካ

• የአሜሪካው የቀድሞ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ አንደኛ የቀብር ስነስርአትን ለመታደም የዓለም መሪዎች እየተሰባሰቡ ነው።

ከ1989 እስከ 1993 ድረስ 41ኛው ፕሬዝዳንት የነበሩት ቡሽ አንደኛ፤ ባለፈው አርብ ነበር ህይወታቸው ያለፈው።

ቻይና

• በቻይና ውስጥ የሚገኝ አንድ ኩባንያ ሰራተኞቹ በወር ውስጥ ከ180 ሺ በታች እርምጃዎች በመራመዳቸው ቅጣት አስተላለፈ።

በደቡባዊ ጉዋንዙ አካባቢ የሚገኝ ስሙ ያልተገለፀ የአንድ ሪል ስቴት ኩባንያ ሰራተኞች የሚጠበቅባቸውን እርምጃ ባለመራመዳቸው በያንዳንዱ እርምጃ 0.1 ሳንቲም ተቀጥተዋል።