ተማሪዎቻቸውን ለማዳን ሲሉ የተሰዉት ሁለቱ ሴት መምህራን

ታትሟል

በአሜሪካ ቴክሳስ ግዛት፣ ዩቫልዲ በምትባል ትንሽ ከተማ፣ ሮብ በሚባል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ አንድ የ18 ዓመት ጎረምሳ በከፈተው የተኩስ እሩምታ 19 ሕጻናትን ገደለ።

ከ19ኙ ሕጻናት ሌላ ሁለቱ መምህራን ተገድለዋል።

ቀን ሲቆጥር፣ እኚህ ሁለቱ መምህራን የሞቱበት ሁኔታ ልብ የሚነካ ሆኖ ተገኘ።

"ደስ የሚል ዓመት ይኖረናል"

ይህን ጽሑፍ በሰሌዳ ላይ የጻፈችው የ4ኛ ክፍል መምህርት ኢርማ ግራሺያ ናት። ግራሺያ ተማሪዎቿን የምትወድ ግሩም መምህርት ነበረች።

ይህ ሰዓት ለክረምት እረፍት ተማሪዎቿን የምታዘጋጅበት ነበር። የቀብር ዝግጅቷ የሚሰናዳበት ወቅት ሆነ። ሕይወት እንዲህ ናት።

ሌላኛዋ መምህርት ኢቫ ማየርለስ ናት። ከግራሺያ ጋር አብረው 4ኛ ክፍል አስተማሪ ነበሩ።

ተኩሱ ሲከፈት ሁለቱ መምህራን ነፍሳቸውን ለማዳን አልሮጡም።

ከዚያ ይልቅ ልጆችን ከጥይት ለመከላከል መሯሯጥ ጀመሩ።

ከሁሉም ልብ የሚነካው ታዲያ መምህርት ግራሺያ በጥይት ተመትታ በተዘረረችበት ወቅት ፖሊሶች በፍጥነት ሲደርሱ ሁለት ሕጻናትን በክንዶቿ እንዳቀፈች ነበር።

ግራሺያ በሞተች በሁለተኛው ቀን ታዲያ ባለቤቷ ጆ ግራሺያ ከፍተኛ ሐዘን በፈጠረው ልብ ድካም ሕይወቱ አለፈ። ድርብ ሐዘን።

ሳቅና ደስታ የማይርቀው 4ኛ ክፍል

ግራሺያ እና ኢቫ ሕይወታቸውን ሙሉ አስተማሪዎች ነበሩ። 4ኛ ክፍል በጋራ ሲያስተምሩ ዘንድሮ 5ኛ ዓመታቸው ነበር።

እነሱ የሚያስተምሩበት ክፍል ሳቅና ጨዋታ ተለይቶት አያውቅም።

በዩቫልዲ የሚኖረው የትምህርት ጉዳዮች ስፔሻሊስት "የከተማችን ብርቅዬዎቹ መምህራን ነበሩ" ይላል።

መምህርት ኢቫ ዕድሜ-44

ኢቫ ለ17 ዓመታት አስተምራለች። መሮጥና ተራራ መውጣት ትወድ ነበር።

"የሚወደኝ ቤተሰብ ስላለኝ ሁሌም ደስተኛ ነኝ" ትል ነበር፣ በተደጋጋሚ።

ከኮሌጅ የተመረቀች ልጅም ነበረቻት። ይህቺ ሴት ልጇ ታዲያ የእናቷን መሞት ተከትሎ ልብ የሚነካ ጽሑፍ በትዊተር ሰሌዳዋ አስነብባለች።

"እናቴ ሞትሽ ሕጻናትን ለማዳን በመሆኑ፣ ያንቺ ምሥልና ጀግንነትሽ በመላው ዓለም በመታየቱ ኮርቼብሻለሁ"

ኢቫ ተኩሱ ሲከፈት ሕጻናቱን ከጥይት ለመከላከል በተኩሱ መሀል ዘላ ገባች።

የተወሰኑ ተማሪዎችን ማዳን ቻለች። ከዚያ ግን ወደማይቀረው ሞት ሄደች።

ኢርማ ግራሺያ፣ ዕድሜ 48

ግራሺያ 23 ዓመት አስተምራለች። ይህን ሁሉ ዓመታት ያስተማረችው ታዲያ ሌላ ቦታ ሳይሆን በሮብ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት ነበር።

በ2019 የትምህርት ቤቱ ምርጥ መምህርት በሚል ተሸልማለች።

የትምህርት ቤቱ ኃላፊዎች እንዳሉት፣ ተኩስ ተከፍቶ ሳለ ግራሺያ ተማሪዎች ለማዳን ለነፍሷ ቅንጣት ሳትሳሳ ወዲያ ወዲህ ስትል ነበር።

ግራሺያ ባለትዳርና የአራት ልጆች እናት ነበረች። ሁለቱ ወንዶች፣ ሁለቱ ሴቶች ናቸው።

የፌስቡክ ገጽዋ በልጆችዋ ፎቶ ያጌጤ ነው።

"ጌታ ሆይ! ከምንም በላይ የሚወደኝ ባልና እነዚህን ውድ ልጆች ስለሰጠኸኝ አመሰግናለሁ" ይላል ከፎቶዎቹ ሥር የጻፈችው።

ይህ የጻፈችው ነገር፣ በተለይም ስለ ባሏ ያለችው ነገር እንዲሁ ለማለት ያህል የተባለ አልነበረም።

ባለቤቷ የእርሷን ሞት ተከትሎ በደረሰበት ከፍተኛ ሐዘን እሱም ተከትሏታል። ወደማይቀረው ሞት።