ኢትዮጵያ ከዓለም በርካታ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ካሉባቸው አገራት አንዷ ሆነች

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተከትሎ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ቀያቸውን ጥለው ተሰደዋል።

የፎቶው ባለመብት, J. Countess

የምስሉ መግለጫ, የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተከትሎ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ቀያቸውን ጥለው ተሰደዋል።
ታትሟል

ኢትዮጵያ ከአምስት ሚሊዮን በላይ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን በመያዝ በዓለም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተፈናቃዮች ካሉባቸው አገራት አንዷ ሆነች።

ኢንተርናል ዲስፕለስመንት ሞኒተሪንግ ሴንተር የተባለው ተቋም የአውሮፓውያኑ 2021 ማብቂያ ላይ በመላው ዓለም የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥር 59.1 ሚሊዮን መድረሱን ገልጿል።

እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ አፍጋኒስታን፣ ሶሪያ እና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ ያሉ አገራት ደግሞ በርካታ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሚገኙባቸው አገራት ናቸው።

በዓለም ላይ በርካታ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሚገኙት ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ብቻ የተመዘገበው 5 ሚሊዮን የተፈናቃይ ሕዝብ ቁጥር በአንድ አገር የተመዘገበ ትልቁ አሃዝ ሆኗል ብሏል ድርጅቱ።

በትግራይ ክልል ተቀስቅሶ አጎራባች ወደሆኑት አማራ እና አፋር ክልሎች ተሸጋግሮ የነበረው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ከቀያቸው ማፈናቀሉ ይታወቃል። ይህንን ጦርነት ተከትሎ በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች የተናቀሉ ሰዎች ቁጥር በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መሆናቸውን የተባበሩት መንግሥታት ገልጾ ነበር።

ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት ከግጭት ጋር ተያይዞ የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር 11.6 ሚሊዮን ሕዝብ ሲሆን ከተፈጥሮ አደጋ ጋር በተያያዘ ደግሞ 2.6 ሚሊዮን ሕዝብ ቀየውን ጥሎ ለመሰደድ ተገዷል።

ዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኮንጎ፣ አፍጋኒስታን እና ሚያንማር እአአ 2021 ላይ ከፍተኛ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን በመመዝገባቸውን የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ቁጥርን የሚከታተለው ማዕከል ገልጿል።

ምንም እንኳ በመካከለኛው ምሥራቅ እና በሰሜን አፍሪካ በሚገኙ አገራት የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥር በ10 ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ቢቀንስም፤ አሁንም በቀጠናው ተፈናቅለው የሚገኙ ሰዎች ቁጥር አሳሳቢ ነው ተብሏል።

ሪፖርቱን ያወጣውን ተቋም በገንዘብ የሚደግፈው የኖርዌጂያን ሪፊዩጂ ካውንስል ዋና ፀሐፊ ያን ኢግላንድ፤ አሁን በዓለማችን ያለው ሁኔታ የበለጠ አሳሳቢ በመሆኑ የተፈናቃዮች ቁጥር እንደሚጨምር ገልጸዋል።

ዋና ፀሐፊው ይህ ሪፖርት በዩክሬን የተፈናቀሉ 8 ሚሊዮን ሰዎችን እንደማይጨምር አስታውሰው፤ የዓለም መሪዎች የሰው ልጆችን ስቃይ መቅረፍ እንዲቻላቸው ግጭቶችን መግታት ስለሚቻልበት ሁኔታ መሠረታዊ የሆነ የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት ይኖርበታል ብለዋል።

እአአ 2021 ላይ 38 ሚሊዮን የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ተመዝግበዋል። ከእነዚህ መካከል 14.4 ሚሊዮን የሚሆኑ ከቀያቸው ለመሸሽ የተገደዱት በግጭት ምክንያት ነው።

የኢንተርናል ዲስፕለስመንት ሞኒተሪንግ ሴንተር ዳይሬክተር አሌክሳንደር ቢላክ፤ በቀደመ መኖሪያ ሰፍራ ዘላቂ እና አስተማማኝ ሁኔታ መፍጠር ካልተቻለ አልያም ተፈናቃዮችን በሌላ አካባቢ ማስፈር ካልተቻለ ለረዥም ጊዜ የዘለቀውን የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጉዳይን መቅረፍ አይቻልም ብለዋል።

"የተፈናቃይ ሰዎችን ሕይወት አጣብቂኝ ውስጥ የከተቱ ችግሮችን ለመፍታት የሰላም ግንባታ እና የልማት ሥራዎች ያስፈልጋሉ" ብለዋል።

እንደ ሪፖርቱ ከሆነ ከግጭት ቀጥሎ ሰዎች ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ እያደረገ ያለው ዋነኛ ምክንያት ከአየር ፀባይ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ አደጋዎች ናቸው።

እአአ 2021 ከተመዘገበው የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች መካከል 23.7 ሚሊዮን የሚሆኑት ቀያቸውን ጥለው የሸሹት ተፈጥሯዊ በሆኑ አደጋዎች ሳቢያ ነው።

ግጭት ከተፈጥሯዊ አደጋ ጋር በመደማማር በበርካታ አገራት በርካቶችን አፈናቅለዋል። የኮቪድ-19 ስርጭትም የተፈናቃዮች ሕይወት ከባድ አድርጎታል ተብሏል።

በዓለማችን ላይ ከተመዘገቡት የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች መካከል ከ25 ሚሊዮን የማያንሱት እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ነው።