ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቱርክ፣ የፊንላንድና ስዊድን ኔቶን የመቀላቀል ሐሳብ እንደምትቃወም ገለጸች
የቱርክ ፕሬዝዳንት ራሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ሁለቱ የስካንዲኒቪያን አገራት ኔቶን ለመቀላቀል የሚያደርጉትን ሩጫ እንደሚቃወሙ ዝተዋል።
ኤርዶጋን ይህን ያሉት ስዊድንና ፊንላንድ ኔቶን ለመቀላቀል በይፋ መወሰናቸውን ባስታወቁ በሰዓታት ውስጥ ነው።
ጣይብ ኤርዶጋን ሁለቱ አገራት የኩርድ ነጻ አውጪዎችን ለማስተናገድ መፍቀዳቸው ሳያስቆጣቸው አልቀረም።
ከኤርዶጋን ቅሬታ ጥቂት ቀደም ብሎ ስዊድን የዩክሬንን ወረራ በአውሮጳ አዲስ ስጋት ለመፈጠሩ ማሳያ መሆኑን ጠቅሳ ለዚህ አዲስ እውነታ አዲስ አስተሳሰብ ያስፈልጋል ብላ ነበር።
የሩሲያው ፑቲን በበኩላቸው ፊንላድና ስዊድን የጦር ቃል ኪዳን ድርጅቱን መቀላቀላቸው ሞስኮን ያን ያህልም እንደማያስጨንቃት፣ ቀጥተኛም ጉዳት እንደማያደርስባት ተናግረዋል።
ይሁንና 30 አባላት ያሉት የጦር ቃል ኪዳን ድርጅቱ መስፋፋት ግን ከክሬምሊን ተመጣጣኝ አጸፋ እንደሚኖረው አስታውቀዋል።
ኤርዶጋን ትናንት ሰኞ በሰጡት በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ የስዊድንን እና የፊንላንድን ወደ ኔቶ መምጣት በበጎ እንደማያዩት ብሎም እንደሚቃወሙት ዝተዋል።
ሁለቱ አገሮች አሸባሪ አቃፊ ናቸው ሲሉም ወርፈዋቸዋል።
"እንዴት ነው እነዚህን አገሮች የምናምናቸው፤ በጉያቸው አሸባሪ ቡድኖችን ያቀፉ ሆነው ሳለ!?" ሲሉ ነው ጣይብ ኤርዶጋን የተናገሩት።
ይህን ተከትሎ ፊንላንድና ስዊድን ኤርዶጋንን ለማሳመን የልኡካን ቡድን ወደ ቱርክ ይልካሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ቱርክ የኩርድ ነጻ አውጪ ፒኬኬን እና የፈቱላህ ጉላን ተከታዮችን በአሸባሪነት ነው የምታያቸው።
አንካራ በተለይ ፈቱላህ ጉላን የ2016 መፈንቅለ መንግሥትን ያቀነባበሩ ናቸው ስትል በጥብቅ ትፈልጋቸዋለች።
ቱርክ ማንኛውም በአገሯ ላይ ማዕቀብ ጥሎ የነበረን አገር ኔቶን እንዳይቀላቀል የተቻላትን እንደምታደርግ ዝታለች።
ፊንላንድና ስዊድን ቱርክ በሶሪያ ላይ እጇን ማስገባቷን ተከትሎ የመሣሪያ ማዕቀብ ጥለው ነበር።
ኖርዌይ፣ ዴንማርክና አይስላንድ ሦስቱም የኔቶ አባላት ሲሆኑ የፊንላንድና የስዊድንን ውሳኔ ከልብ እንደግፈዋለን ብለዋል።
ዩኬ ለሁለቱ አገራት የደህንነት ከለላን እሰጣለሁ ብላለች።
ኔቶ በዚህ ሰዓት መጠነ ሰፊ የጦር ልምምድ በባልቲክ አካባቢ እያደረገ ሲሆን 15ሺህ ወታደሮችን ያሳተፈ ነው። ይህ የጦር ልምምድ በኢስቶኒያ ነው የተጀመረው።