ፕሪሚየር ሊግ፡ ማን ዋንጫ ያነሳል? ማንስ ከሊጉ ይወርዳል?

ታትሟል

በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ለዋንጫ ከሚደረገው ፉክክር በተጨማሪ በአውሮፓ መድረክ ለመሳተፍ እና ላለመውረድ የሚደረገው ትግል እስከ መጨረሻው ሳምንት ድረስ እንደሚዘልቅ እውን ሆኗል።

15 ጨዋታዎች ቀርተዋል። እሁድ የሊጉ ጨዋታዎች ከመጠናቀቃቸው በፊት ሰኞ (ዛሬ) ፣ ማክሰኞ እና ሐሙስ የሚከናወኑ ተስተካካይ ጨዋታዎች አሉ።

የትኛው ቡድን ምን ይፈልጋል?

የዋንጫ ፉክክር

ማክሰኞ፡ ሳውዝሃምፕተን ከሊቨርፑል

እሑድ፡ ሊቨርፑል ከዎልቭስ እና ማንቸስተር ሲቲ ከአስቶን ቪላ

ማንቸስተር ሲቲ ትላንት እሁድ ከዌስት ሃም ጋር ሁለት አቻ ተለያይቷል። አሁንም ግን ሊጉን በበላይነት ከመምራት አላገደውም። ቀሪ ጨዋታውን ካሸነፈ በአምስት ዓመት ውስጥ አራተኛ የሊግ ዋንጫውን ከፍ አድርጎ ይስማል።

ሲቲ እስከ እሁድም ላይጠብቅ ይችላል። ማክሰኞ ሴንት ሜሪ ላይ ሊቨርፑል ከተሸነፈ ዋንጫው ኢትሃድ መድረሱ ይረጋገጣል።

ዋንጫውን ለማንሳት ሊቨርፑል ቀሪዎቹን ሁለት ጨዋታዎች ማሸነፍ ይገባዋል። ማንቸስተር ሲቲም በእሁዱ ጨዋታ ከአስቶን ቪላ ጋር ነጥብ መጣሉ መረጋገጥ አለበት።

"ሊቨርፑልን የመሰለ ቡድን እያለ አራት ጨዋታዎች እየቀሩ ዋንጫ ማንሳት ከባድ ነው። እስከመጨረሻው ፉክክሩ ይቀጥላል። እኛን የሚጠቅመን በሜዳችን መጫወታችን እና የሚወሰነውም በራሳችን መሆኑ ነው" ያለው የሲቲው አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ነው።

"ማንንም አንመለከትም። ራሳችን ጨዋታውን ለማሸነፍ እንሞክራለን። ኢትሃድ ስታዲም እንደሚሞላ እና ደጋፊው ከጎናችን እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ።"

ከማክሰኞው ጨዋታ በፊት ለሳውዝሃምፕተን መልዕክት ካለው ሲጠየቅም "ሊቨርፑልን 4 ለ 0 አሸንፉ" ብሏል።

በቻምፒዮስ ሊግ ለመሳተፍ የሚደረገው ፉክክር

ሰኞ፡ ኒውካስል ከአርሴናል

ሐሙስ፡ ቼልሲ ከሌስተር

እሑድ፡ አርሴናል ከኤቨርተን፣ ቼልሲ ከዋትፎርድ እና ኖርዊች ከስፐርስ

አርሴናል ቀሪዎቹን ሁለት ጨዋታዎች ማሸነፍ ከቻለ ከ2016/17 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የቻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ ይሆናል።

ነጥብ ከጣለ ግን ስፐርስ መውረዱን ያረጋገጠውን ኖርዊችን ማሸነፍ ብቻ የአውሮፓ ትልቁ ውድድር ተሳታፊ ያደርገዋል።

"እንግሊዝ ውስጥ የቻምፒዮንስ ሊግ ቦታ በጣም ወሳኝ ነው። በሌላ ሊግ ትልቅ ዋንጫ እንደማንሳት ይቆጠራል" ያለው ስፐርሱ አሰልጣኝ አንቶኒዮ ኮንቴ ነው።

"አርሴናል ዛሬ ይጫወታል። ለጊዜው በሁለት ነጥብ እንበልጣቸዋለን። ካላሸነፉ ዕጣችንን የምንወስነው ራሳችን ነን። ለጊዜው ግን ኳሱ ያለው በእነሱ እጅ ነው።"

"የመጨረሻው ጨዋታ ለእኛ ወሳኝ ነው። እንግሊዝ ውስጥ ቀላል ጨዋታ የለም። ወደ ኖርዊች አቅንተን አሸንፈን ሦስት ነጥብ ማግኘት አለብን።"

ቼልሲ የቻምፒዮንስ ሊግ ቦታውን ሊያጣ ይችላል። ከሌስተር እና ከዋትፎርድ በሚቀሩት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ካገኘ በቂው ነው።

ለዩሮፓ ሊግ እና ለኮንፈረንስ ሊግ የሚደረገው ፉክክር

ድ፡ ብራይተን ከዌስት ሃም እና ክሪስታል ፓላስ ከማንቸስተር ዩናይትድ

ዌስት ሃም እና ማንቸስተር ዩናይትድ በሚቀጥለው ዓመት በአውሮፓ መድረክ እንደሚሳተፉ አረጋግጠዋል። ጥያቄው በየትኛው መድረክ የሚለው ነው።

ማንቸስተር ዩናይትድ በመጨረሻው ጨዋታ ክሪስታል ፓላስን ካሸነፈ የዩሮፓ ሊግ ተሳታፊነቱን ያረጋግጣል። ዌስት ሃም ደግሞ በኮንፈረንስ ሊግ ይሳተፋል።

ዌስት ሃም አሸንፎ ማንቸስተር ዩናይትድ ማሸነፍ ካልቻለ ግን የለንደኑ ክለብ ወደ ዩሮፓ ሊግ ዩናይትድ ደግሞ ኮንፈረንስ ሊግ ያመራሉ።

"ስድስተኛ ሆነን ካጠናቀቅን ትልቅ ስኬት ነው። ሰባተኛ መሆንም ትልቅ ነው። ስድስተኛ መሆን ከቻልን ግን የበለጠ ጥሩ ነው። በሚቀጥለው ሳምንት እንደምናሳካው ተስፋ አለኝ። ለማሳካትም እንሞክራለን።"

ላለመውረድ የሚደረገው ፉክክር

ሐሙስ፡ ኤቨርተን ከክሪስታል ፓላስ እና አስቶን ቪላ ከበርንሌይ

ድ፡ አርሴናል ከኤቨርተን፣ በሬንትፎርድ ከሊድስ እና በርንሌይ ከኒውካስል

ሐሙስ ዕለት የሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች የሚወርዱ ቡድኖችን ዕጣ ይወስናል።

ኤቨርተን፣ ሊድስ እና በርንሌይ በሁለት ነጥብ ተለያይተው ተቀምጠዋል። በርንሌይ በወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ተስተካካይ ጨዋታ ይቀረዋል። በዚህም የሊድስ ዕጣ ፈንታ በሌሎች ይወሰናል።

የፍራንክ ላምፓርድ ቡድን ትላንት እሁድ ከብሬንትፎርድ ያደረገው ጨዋታ አሸንፎ ቢሆን እንደማይወርድ ያረጋግጥ ነበር። ሐሙስ ፓላስን ካሸነፉም በተመሳሳይ ያረጋግጣሉ።

"ሐሙስም ያለንን በሙሉ መስጠት አለብን። እስከመጨረሻው እንታገላለን። ዕጣችን እጃችን ነው" ብሏል።

በርንሌይ ሐሙስ ምሽት አስቶን ቪላን ገጥሞ ካሸነፈ ከወራጅ ቀጠና ይወጣል።

"በደጋፊያችን ፊት እንደምንጫወት እናውቃለን። ነጥብ ማግኘት አለብን" ያለው የበርንሌይ ተጠባባቂ አሰልጣኝ የሆነው ማይክ ጃክሰን ነው።

"በጣም ግልጽ ነው። መሸፋፈን አያስፈልግም። ቀጣዩን ጨዋታ ማሸነፍ አለብን።"

የሊድስ እና የበርንሌይ ፉክክር እስከ መጨረሻው ሳምነት ይቀጥላል። ሊድስ በሬንትፎርድ ሲጫወት በርንሌይ ደግሞ ኒውካስልንን ያስተናግዳል። ቶፎዎቹ ሐሙስ ማሸነፍ ካልቻሉ በመጨረሻው ሳምንት ከአርሴናል ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ከባድ ይሆናል።

"በርንሌይ ተስተካካይ ጨዋታ አለው። ትላንት አንድ ነጥብ ማግኘታችን ተጽዕኖውን ወደ እነሱ ያዞረዋል" ያለው የሊድሱ አሰልጣን ጄሲ ማርሽ ነው።

"ያለነው የሥነ-ልቦና ጦርነት ውስጥ ነው። በሚቀጥለው ሳምንት ያለንን ሁሉ ማውጣት አለብን። ለዚህም ተዘጋጅተናል። ያለንን በሙሉ ለመጨረሻው ጨዋታ አዘጋጅተናል።"