ሕንድ ውስጥ በአንድ ህንጻ ላይ በተነሳ የእሳት አደጋ ቢያንስ 27 ሰዎች ሞቱ

ታትሟል

በሕንድ ዋና ከተማ ደልሒ በአንድ ባለአራት ፎቅ የቢሮ ህንጻ ላይ በተነሳ የእሳት አደጋ ቢያንስ 27 ሰዎች ሲሞቱ፣ በ12 ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን የእሳት እና ድንገተኛ አደጋዎች አገልግሎት አስታወቀ።

የእሳት አደጋው ሲነሳ ከ70 ሰዎች በላይ በህንጻው ውስጥ የነበሩ ሲሆን፣ ፖሊስ የህንጻውን መስኮቶች በመስበርና ገመድ በመዘርጋት የቀሪ ሰዎችን ሕይወት መታደግ መቻሉ ተነግሯል።

የአብዛኞቹ ሟቾች አስክሬኖች የተገኙት በህንጻው ሁለተኛ ፎቅ ላይ ነው ተብሏል።

በዋና መዲናዋ ደልሒ በሙንዱካ ባቡር ጣቢያ አቅራቢያ የተነሳውን ይህንን እሳት ለማጥፋት 20 የእሳት ማጥፊያ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት ላይ ውለዋል።

የአደጋው መንስኤ በህንጻው ውስጥ የተዘረጋ የኤሌክትሪክ መስመር ችግር እንደሆነም ተገልጿል።

የሕንድ መገናኛ ብዙኃን ከአደጋው ጋር በተያያዘ ሁለት ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ዘግበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በአደጋው ምክንያት በደረሰው ጉዳት ማዘናቸውን ገልጸው፣ ለእያንዳንዱ ሟች ቤተሰቦች 200 ሺህ ሩፒ ( 2 ሺህ 580 ዶላር) ካሳ ለመክፈል ቃል ገብተዋል።

እሳቱ ከጠፋ በኋላ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ነፍስ የማዳን ሥራቸውን እንደቀጠሉ እና ሰፊ የሆነውን የአደጋውን አካባቢው ለመቆጣጠር ጊዜ እንደሚወስድ 'ታይምስ ኦፍ ኢንዲያ' ጋዜጣ የእሳት አደጋ ምክትል ኃላፊ ሰኒል ቾድሃሪን ጠቅሶ ዘግቧል።

የአካባቢው ባለሥልጣን ጆጊ ራም ጄን የኤሌክትሪክ ችግር ለእሳት አደጋው መንስኤ እንደሆነ እና ህንጻው አስፈላጊ የሆኑ የእሳት ደኅንነት ማረጋገጫ እንዳልነበረው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቶች እንዳመለከቱ ገልጸዋል።

"ምርመራ ጀምረናል፤ የማንኛውም ባለሥልጣን ስህተት ከሆነ ተገቢውን እርምጃ እንወስዳለን " ሲሉ ጆጊ ለ'ሂንዱስታን ታይምስ' ጋዜጣ ተናግረዋል።