የግብፅ ፒራሚድን በመጎብኘት ላይ የነበሩ ሴት ጎብኚዎችን የተነኮሱ 13 ታዳጊዎችን ታሰሩ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በግብፅ በጉብኝት ላይ የነበሩ ሴት ቱሪስቶችን ተንኩሰዋል ተብለው የተጠረጠሩ አስራ ሦስት ታዳጊዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ።
በጊዛ ፒራሚድ በጉብኝት ላይ የነበሩ ሁለት ሴት የውጭ ጎብኚዎችን ሲተነኩሱ ነበሩ የተባሉት ታዳጊዎች በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ትዕዛዝ ያስተላለፈው የግብፅ ዐቃቤ ሕግ ነው።
ባለፈው ሳምንት ታዳጊዎቹ በቡድን ሆነው በአገሪቷ የሚገኘውን ታሪካዊ ቦታ ሲጎበኙ የነበሩ ሁለት ወጣት ሴቶችን ሲተነኩሱ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ከተጋራ በኋላ ግብፃውያን ቁጣቸውን ገልጸዋል።
ዐቃቤ ሕግ ይህንን ተከትሎ ባወጣው በመግለጫ ላይ እንዳለው ታዳጊዎቹ ከ13 እስከ15 በሚሆን የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው።
ታዳጊዎቹ በበኩላቸው ከጎብኚዎቹ ጋር ፎቶ ለመነሳት ፈልገው እንጂ ምንም አይነት ችግር መፍጠር ፈልገው እንዳልነበረ ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ በእነርሱ ላይ የሚካሄደው ምርመራው እስከሚጠናቀቅ ድረስ በታዳጊዎች ማረሚያ ማዕከል ውስጥ እንደሚቆዩ ዐቃቤ ሕግ በመግለጫው አስታውቋል።
ዐቃቤ ሕግ በመግለጫው አክሎም ጎብኚዎቹ በታዳጊዎቹ ላይ ካቀረቡት ክስ በተጨማሪ፣ ታዳጊዎቹ ሴት ጎብኚዎቹን ቃላዊ እንዲሁም አካላዊ ትንኮሳ ሲፈፅሙ የሚያሳይ በአስጎብኚ የተቀረፀ ተንቀሳቃሽ ምስል እንዳለም ገልጿል።
የ35 ሰከንዶች ርዝማኔ ያለው ተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ አስጎብኚው "ግብፃውያን ታዳጊዎች የውጭ ጎብኚዎች ሥር ሥር መሄዳቸውን" ሲያማርር እና ይህንንም ለቱሪዝም ሚኒስቴር ማሳወቅ እንደሚፈልግ ሲናገር ይሰማል።
ታዳጊዎቹ ደግሞ ሞባይል ስልክ ይዘው ሴቶቹን ሲከቧቸው እና አንደኛዋ ሴት ጎብኚ አንድ ከፊት ለፊቷ የነካትን ታዳጊ ለመከላከል ስትገፋው ያሳያል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በግብፅ በሚቱ [#Me too] በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን በሚቃወመው ዓለም አቀፍ ዘመቻ የተነሳሱ በርካታ ሴቶች የሚደርስባቸውን ወሲባዊ ጥቃት እና ትንኮሳ በማኅበራዊ ሚዲያ ወጥተው አያሳወቁ ይገኛሉ።
ባለፈው ዓመትም የአገሪቷ ምክር ቤት ቀደም ሲል የነበረውን የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ በማሻሻል ወሲባዊ ትንኮሳ የሚፈፅሙ ሰዎች ላይ ከባድ ቅጣት እንዲተላለፍ የቀረበውን ሕግ አጽድቋል።
በዚህም መሠረት ድርጊቱን በፈፀሙ ላይ ከ6 ሺህ 370 እስከ 12 ሺህ 740 ዶላር የገንዘብ ቅጣት በተጨማሪ ቀድሞ የነበረው ቢያንስ የስድስት ወር እስር ወደ ሁለት ዓመት እስር ከፍ ተደርጓል።
ሆኖም የግብፅ ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ በሴቶች እና በልጃገረዶች ላይ ወሲባዊ ትንኮሳ በሚፈፅሙ ወንዶች ላይ ተገቢውን ምርመራ አድርገው የቅጣት ውሳኔ ማስተላለፍ ባለመቻላቸው ይከሰሳሉ።
እአአ በ2013 የወጣ የተባበሩት መንግሥታት ጥናት፣ በግብፅ 99.3 በመቶ የሚሆኑ ሴቶችና ልጃገረዶች በሕይወት ዘመናቸው ወሲባዊ ትንኮሳ እንደደረሰባቸው፣ እንዲሁም 82.6 በመቶ የሚሆኑት ደኅንነት እንደማይሰማቸው ወይም በመንገድ ላይ ደኅነንታቸው የተጠበቀ እንዳልሆነ አመልክቷል።












