11 የግብፅ ወታደሮች በሲናይ በረሃ በአይኤስ ታጣቂዎች ተገደሉ

ታትሟል

የእስላማዊ ቡድን (አይኤስ) ታጣቂ ቡድን አባላት ቅዳሜ ሚያዚያ 29/2014 ዓ.ም. በሲናይ በረሃ ውስጥ በፈጸሙት ጥቃት 11 የግብፅ ወታደሮች ተገደሉ።

በጥቃቲ አንድ የጦር መኮንንና 10 ወታደሮች መገደላቸውን የግብፅ ጦር ኃይል ቃል አቀባይ አመልክተው፣ ጥቃቱ የተፈጸመው በአንድ የፍተሻ ኬላ አካባቢ በሚገኝ ውሃ ማውጫ አካባቢ ነው ብለዋል።

ለጥቃቱ ጸንፈኛው አይኤስ ኃላፊነቱን የወሰደ ሲሆን፣ ይህ በሰሜናዊ ሲናይ በረሃ በግብፅ ጦር ላይ የተፈጸመው ጥቃት ከዓመታት በኋላ በርካታ ወታደሮች የተገደሉበት ክስተት ነው ተብሏል።

በዚህ አካባቢ የግብፅ ወታደሮች ከእስላሚክ ስቴት ጋር ግንኙነት ያላቸውን ታጣቂዎች ሲዋጉ ቆይተዋል።

በግብፅ ወታደሮች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ አውግዘው፣ ሕብረቱ ከግብፅ መንግሥት እና ሕዝብ ጎን እንደሚቆም ገልጸዋል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል በስም ያልጠቀሳቸውን የደኅንነት ምንጮች ዋቢ አድርጎ ባወጣው ዘገባ፤ ታጣቂዎቹ መኪና ላይ በተጠመደ ቦምብ እና ፒክ አፕ መኪና ላይ በጠመደ ከባድ መሳሪያ የግብፅ ወታደሮች ላይ ጥቃት ፈጽመዋል።

ተጨማሪ የግብፅ ሠራዊት ጥቃቱን መክቶ ታጣቂዎቹን ማሳደዱን የሮይተርስ ዘገባ አመልክቷል።

የግብጽ ጦር ቃል አቀባይ ግሃሪብ አበደላ ሃፌዝ ከተገደሉት 11 የጦር ሠራዊት አባላት በተጨማሪ 5 ሰዎች መጎዳታቸውን ገልጸዋል።

የግብፅ ጦር ከእአአ 2018 ጀምሮ በሰሜን ሲናይ፣ በምሥራቅ ጋዛ ሰርጥ እና በምዕራብ ሱዊዝ ካናል ቁጥጥሩን አስፋፍቷል።

ይሁን እንጂ ጸንፈኛ ታጣቂ ቡድኖች በጦር ኃይሉ ላይ ተቀጣጣይ ፈንጂዎችን በመቅበር እና ከርቀት ሆነው ተኩስ በመክፈት ጥቃት ሲያደርሱ ቆይተዋል።