ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሩሲያ የጠፈር ማዕከል የተገኘው እንግሊዛዊው ዩቲዩበር ምርመራ ተደረገበት
ፍቃድ ሳይሰጠው በሩሲያ የጠፈር ማዕከል የተገኘው እንግሊዛዊው ዩቱበር ምርመራ ተደረገበት።
ቤንጃሚን ሪች የተባለው ዩቲዩበር በካዛክስታን በሚገኘው የሩሲያ የጠፈር ማዕከል "ለሰዓታት" በፖሊስ ምርመራ እንደተደረገበት ገልጿል።
በቀድሞዋ የሶቪየት ሕብረት አባል አገር በነበረችው ካዛክስታን ባለው የጠፈር ማዕከል ውስጥ ፈቃድ ሳይዝ ቀረጻ አድርጓል የተባለው ቤንጃሚን በሩሲያ ፖሊሶች ታስሮ ምርመራ ከተደረገበት በኋላ ተለቋል።
ምርመራ ከተደረገበት በኋላ 60 ፓውንድ የተቀጣው ቤንጃሚን ሪች፤ የጠፈር ማዕከሉን ለመጎብኘት የሚያስፈልገውን ልዩ ፈቃድ ባለመያዙ ለቅጣት መዳረጉን ተናግሯል።
የሩሲያው የህዋ ምርምር ተቋም 'ሮስኮስሞስ' ግለሰቡ ሮኬቶች ከሚወነጨፉት ማዕከል ውስጥ በመገኘቱ በቁጥጥር ስር መዋሉን መገለጹ ይታወሳል።
ተቋሙ አክሎም ሪች "ሕገ ወጥ ተግባራትን" መፈጸሙን ተከትሎ ምርመራ እየተደረገበት ነው ብሎም ነበር።
የጉዞ ቪዲዮዎችን በመስራት የሚታወቀው ዩቲዩበሩ ግን በኢንስታግራም ልጥፉ ላይ "የሩሲያ ፖሊሶች ለጥቂት ሰዓታት የቡራን ሮኬትን ያለ ልዩ ፈቃድ ለማየት በመሄዴ ጥያቄዎችን አቅርበውልኛል። ከእኔ በፊት እንደነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ደፋር ጎብኚዎች ሁሉ የ60 ፓውድ የአስዳደር ቅጣት ተቀጥቼ በነጻ ተሰናብቻለሁ" ሲል አስፍሯል።
ሪች አክሎም "ልክ በተከለከለ ቦታ ላይ እንደማጨስ አይነት 'እንዳይለመድህ' የሚል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶኛል" ሲልም ተናግሯል።
ቤንጃሚን ሪች ከ3.5 ሚሊዮን በላይ ተከታታዮች ያሉት የዩቲዩብ ገጽ አለው።
ይህ ወደጠፈር መምጠቂያ ማዕከል ወደ ጠፈር የሚመጥቁ የሩሲያ ሮኬቶች መነሻ ሲሆን፣ ከሩሲያው የጠፈር ጉዳዮች ተቆጣጣሪ ድርጅት ሮስኮስሞስ ፈቃድ ለሚያገኙ ቱሪስቶች ለጉብኝት ክፍት ነው።