ቼልሲ ቡድኑን ለአሜሪካው ባለሃብት ቶድ ቦህሊ ለመሸጥ ስምምነት ላይ ደረሰ

ታትሟል

የቼልሲ እግር ኳስ ክለብ፣ በአሜሪካ ሎስ አንጀለስ በሚገኘውና የቤዝቦል ቡድን አንዱ ባለቤት በሆኑት ቶድ ቦህሊ ለሚመራው ጥምረት 5.2 ቢሊየን ዶላር ለመሸጥ የሚያስችል ስምምነት ላይ መድረሱ ተገለጸ።

ቼልሲ ለሽያጭ የቀረበው የቡድኑ ባለቤት ሮማን አብራሞቪች የዩክሬንን ጦርነት ተከትሎ ከሩሲያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ማዕቀብ ሳይጣልባቸው በፊት ነበር።

ባለሃብቱ አብራሞቪች ከወራት በፊት በፕሪሚየር ሊጉ ክለብ ድረ-ገጽ ላይ ባወጡት መግለጫ ስለ ቼልሲ መሸጥ "በጣም ከባዱን እና የሚያመውን ውሳኔ" መወሰናቸውን ተናግረዋል።

አብራሞቪች በዩናይትድ ኪንግደም ፓርላማ የማዕቀብ ስጋት "ቼልሲን በፍጥነት ለመሸጥ" እንደፈለጉ እና ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው የተነገረ ሲሆን እሳቸው ግን ይህንን አስተባብለዋል።

ቼልሲን ለመግዛት የተስማሙት አዲሶቹ የክለቡ ባለቤቶች ለክለቡ ባለአክሲዮኖች 2.5 ቢሊየን ፓውንድ እንደሚከፍሉ ተነግሯል።

ይህ ገንዘብም ለበጎ አድራጎት ለመለገስ ወደማይንቀሳቀስ የሂሳብ ቁጥር ይገባል ተብሏል።

ጥምረቱ በአሜሪካዊው ባለሃብት ቦህሊ እንዲሁም ክሊርሌክ ካፒታል ግሩፕ፣ ማርክ ዋልተር እና በስዊትዘርላንዳዊው ቢሊየነር ሀንስዮርግ ዋይስ የሚመራ ሲሆን በፕሪሚየር ሊጉ ክለብ ላይ ኢንቨስት ለማድረግ 1.75 ቢሊየን ፓውንድ እንደሚያቀርቡ ተልጿል።

ቼልሲ በመግለጫው ላይ እንዳለው ሽያጩ በግንቦት ወር መጨረሻ ላይ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

የክለቡ ርክክብም ከእንግሊዝ የእግር ኳስ ባለሥልጣናት እና ከዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ፈቃድ ያስፈልገዋል ተብሏል።

ቦህሊ አሜሪካዊ ባለሃብት እና የንግድ ሰው ሲሆን 4.5 ቢሊየን ዶላር የተጣራ ሃብት እንዳላቸው ፎርብስ ዘግቧል።

ባለሃብቱ ቦህሊ በሎስ አንጀለሱ የቤዝቦል ክለብ፣ ዶጀርስ፣ በአሜሪካ የሴቶች ቅርጫት ኳስ ቡድን [ሎስ አንጀለስ ስፓርክስ] ባለቤት ሲሆኑ በታዋቂው የቅርጫት ኳስ ቡድን በሎስ አንጀለስ ሌከርስ ውስጥም የባለቤትነት ድርሻ አላቸው።