የዩኬ ፖሊስ ድንበር ሊያቋርጡ የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ያዘ

ታትሟል

የብሪታኒያ ድንበር ጠባቂ ኃይል ኢንግሊሽ ቻናል ተብሎ በሚጠራው የውሃ ክፍል በኩል ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ለመግባት የሞከሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ይዟል።

የአገሪቱ መከላከያ ወደ ዩኬ ለመግባት የሞከሩ ስደተኞችን ቁጥር እስካሁን ባይገልጽም ቢቢሲ በአካባቢው ከነበሩ ሰዎች የስደተኞቹ ቁጥር ከ200 በላይ መሆኑን ሰምቷል።

ስደተኞቹ የኢንግሊሽ ቻናል ሲያቋርጡ ይህ ከ11 ቀናት በኋላ የመጀመሪያው ነው።

ዩኬ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከፈረንሳይ ተነስተው በኢንግሊሽ ቻናል በኩል የሚሻገሩ አብዛኛውን ስደተኞች ወደ ሩዋንዳ እልካለሁ ካለች በኋላ ወደ አገሪቱ የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር ቀንሷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን የአገሪቱ መከላከያ አነስተኛ ጀልባዎችን በመጠቀም የሚሻገሩ ስደተኞችን የመግታት ኦፕሬሽን እንዲያካሂድ ኃላፊነት ተሰጥቶታል ብለው ነበር።

የዩኬ መከላከያ በአንድ ግዜ በርካታ ስደተኞች ወደ ዩኬ ለመግባት ጥረት ማድረጋቸውን "አደገኛ" ሲል ገልጾታል።

ባለፉት 4 ወራት በፈረንጆቹ 2022 ማለት ነው፤ አንስተኛ ጀልባዎችን በመጠቀም ወደ ዩኬ የተሻገሩ ሰዎች ቁጥር ከ6ሺህ በልጧል።

እአአ 2021 እንግሊሽ ቻናልን የተሻገሩ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 28ሺህ 526 ነው።

የዩኬ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ የመላክ እቅድ

ዩኬ በኢንግሊሽ ቻናል በኩል እና በደረቅ ጭነት መኪኖች ተደብቀው ወደ ዩኬ የሚገቡ አብዛኛዎቹን ጥገኝነት ጠያቂዎችን በነጠላ የአውሮፕላን ቲኬት ወደ ሩዋንዳ እሸኛለሁ ብላለች።

ቦሪስ ጆንሰን ይህን የመንግሥታቸውን እቅድ ይፋ ሲያደርጉ፤ እርምጃው የበርካታ ሰዎችን ሕይወትን ከሕገ ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች እንደሚታደግ ገልጸው፤ ዩኬ ሁሉንም ስደተኛ ተቀብላ የማስተናገድ አቅሙ እና ፍላጎቱ እንደሌላት አመላክተዋል።

በቀጣይ ዓመታትም አፍሪካዊቷ አገር ሩዋንዳ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን የመቀበል አቅም እንዳላት የዩኬ መሪዎች ገልጸዋል።

በስምምነቱ መሠረት ሩዋንዳ ከዩኬ የምትቀበላቸውን ስደተኞች የጥገኘነት ጥያቄ ትመረምራለች።

የስደተኛው የጥገኘነት ጥያቄ ምላሸ የሚያገኝ ከሆነ በሩዋንዳ እንዲኖር ይፈቀድለታል። በሩዋንዳ የመኖር ፍላጎት የሌለው ስደተኛ ወደ ትውልድ አገሩ ወይም ሊቀበለው ወደሚችለው ሦስተኛ አገር ሊዘዋወር ይችላል።

የስደተኞች መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች የዩኬ መንግሥት እቅድን አጥብቀው ተችተዋል።