በደቡብ አፍሪካው የጎርፍ አደጋ ከ440 በላይ ሰዎች ሕይወታቸው አለፈ

በፍርስራሽ የተዋጠች መኪና

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

ደቡብ አፍሪካ ባለፈው ሳምንት በክዋዙሉ ናታል ግዛት በደረሰው የጎርፍ አደጋ ሳቢያ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች የእርዳታ እና የነፍስ አድን ሥራዎችን ለመስራት ከ10 ሺህ በላይ ወታደሮችን ልታሰማራ እንደሆነ የአገሪቷ ጦር አስታወቀ።

በአደጋው ከ440 በላይ ሰዎች ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን እስካሁን የጠፉ 63 ሰዎችን የመፈለግ ሥራው እንደቀጠለ ነው።

መንግሥት ግዛቷ የአደጋ አካባቢ እንደሆነች ያወጀ ሲሆን ባለሥልጣናት ከዚህ ቀደም በግዛቷ ከተከሰቱ የጎርፍ አደጋዎች አስከፊው እንደሆነ ገልጸዋል።

የግዛቷ አስተዳዳሪ ሲህል ዚካላላ እንዳሉት በአደጋው በባህር ዳርቻዋ ከተማ ደርባን እና አካባቢዋ አራት ሺህ የሚጠጉ ቤቶች ወድመዋል፤ ከስምንት ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ፈራርሰዋል።

በፍለጋ ሥራው ላይ ፖሊስና ጦር ሠራዊቱ የተሳተፉ ሲሆን እሁድ ዕለት ተጨማሪ ስድስት አስክሬኖች መገኘታቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

የደርባን ነዋሪ የሆነችው አማንዳ አቼምፖንግ የእህቷ እና ሦስት የልጅ ልጆቿ አስክሬን በወንዙ ዳርቻ መገኘቱንና ቀሪዎቹ ስድስት ዘመዶቿ ግን እስካሁን አለመገኘታቸውን ተናግራለች።

ሌላኛዋ ነዋሪ ሌትዌ ሲቢያም የእህቷን ልጅ እስካሁን አላገኘችውም። ሌሎች ነዋሪዎችም የጠፋባቸውን የቤተሰብ አባል በማፈላለግ ላይ ናቸው።

የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ መከላከያ ኃይል በሰጠው መግለጫ ወታደሮቹ የፍለጋ እና የነፍስ ማዳን ሥራዎችን እንደሚያጠናክሩ እና ለተጎጂዎች እርዳታን በማጓጓዝ ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታውቋል።

የሠራዊቱ የቧንቧ እና የኤሌክትሪክ ሰራተኞችም ለአንድ ሳምንት ያህል ውሃ እና መብራት በሌለባቸው አካባቢዎች እንደሚሰሩ መሥሪያ ቤቱ በመግለጫው አክሏል።

በአደጋው የተወሰኑ ማኅበረሰቦች መንገዶችና ድልድዮች በመፈራረሳቸው ከሌሎቹ አካባቢዎች ጋር ያላቸው ግንኙነት ተቋርጧል።

ወደ 300 የሚጠጉ ትምህርት ቤቶች እና የተወሰኑ የጤና ተቋማትም በጎርፉ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

የግዛቷ አስተዳዳሪ ዚካላላ ነዋሪዎች በወንዝ ዳርቻዎች ላይ ቤቶችን ከመሥራት እንዲቆጠቡም አሳስበዋል።

ባለፈው ሳምንት ፕሬዚደንት ሲሪል ራማፎሳ በጎርፍ የተጎዱ አካባቢዎችን በጎበኙበት ወቅት በአደጋው የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባትና የተጎዱ ቤተሰቦችን ለመደገፍ ወደ ኋላ እንደማይሉ ቃል ገብተዋል።

ከፈራረሰ ቤት አጠገብ የቆሙ ግለሰብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአየር ሁኔታ ባለሙያዎች፣ የአየር ንብረት ለውጥ እንደዚህ ያሉ አስከፊ ክስተቶች የበለጠ እንዲደጋገሙ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።

አሁን ላይ የዝናቡ መጠን እየቀነሰ ቢሆንም ባለፈው ሰኞ የጣለው የዝናብ መጠን ከአገሪቷ አማካይ ዓመታዊ የዝናብ መጠን 75 በመቶው ጋር እኩል ነው።

ጎርፉን ያስከተለው የአየር ሁኔታ ባለፈው ሚያዝያ 3 ቀን በ24 ሰዓታት ውስጥ በ300 ሚሊ ሜትር የተለካ ዝናብ ያዘነበ ሲሆን ቀድሞ ከነበሩት ጋር ሲነጻጸር እጅግ ከፍተኛው ሆኖ ተመዝግቧል።

እአአ በ2019 ሚያዝያ ወር ላይ የጣለው ከፍተኛ ዝናብ 165 ሚሊ ሜትር የተለካ ሲሆን ከዚያ ቀደም ብሎ በ2017 ጥቅምት ወር ላይ የተመዘገበው ከፍተኛው የዝናብ መጠን 108 ሚሊ ሜትር ነበር።