ደቡብ አፍሪካ ጎርፍ፡ "ቤቴ ምንም አይሆንም ብዬ አስቤ ነበር"

የፎቶው ባለመብት, BBC / CAMILLA MILLS
በደቡብ አፍሪካ ኩዋዙሉ ናታል ግዛት ለቀናት የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በተከሰተው ጎርፍ የጠፉ ሰዎችን የመፈለጉ ሥራ አሁንም እንደቀጠለ ነው።
የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በሕይወት የተረፉ ሰዎችን ለመፈለግ በሚያደርጉት ጥረት በመንገዳቸው ላይ ዝናብ በመኖሩ ፍለጋቸውን አዳጋች አድርጎባቸዋል።
ሂሮ ካንጋታ የደርባን ነዋሪ ነው። በጎርፉ ምክንያት ለዘመናት የደከመበትን ቤቱን አጥቷል።
"ቤቴ እዚህ ነበር። ወንዙ ከቤቴ ጀርባ ስድስት ወይም ሰባት ሜትር ርቀት ላይ ነበርና ቤቴ ምንም አይሆንም ብዬ አስቤ ነበር" ይላል ሂሮ ካንጋታ በደርባን የሚገኘውን ቤቱን ፍርስራሽ እያመላከተ።
" በጣም ተጨንቄያለሁ። ምን እንደማደርግ አላውቅም። የት እንደምሄድም አላውቅም። ወደፊት የሚሆነውን አላውቅም። በእውነቱ ወደፊት የሚታየኝ ምንም ነገር የለም" ይላል።
ሂሮ በጎርፉ ሳቢያ ጉዳት ካጋጠማቸው 40 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች አንዱ ነው።
ባለሥልጣናት እንደሚሉት 13 ሺህ 500 ቤቶች ወድመዋል። በርካቶችም ቤት አልባ ሆነው ያለመጠለያ፣ ምግብ እና ውሃ ቀርተዋል።
ከሂሮ ቤት አቅራቢያው ያለች አንዲት ሴት በበኩሏ ቤቷ ከመፍረሱ በፊት መሸሽ እንዳለባት ተናግራለች።
" አሁን የማርፍበት ቦታ እፈልጋለሁ። አሁን ለልጆቼ ደህንነት ስል እየወጣሁ ነው። በጣም ከባድ ነው ግን በሕይወት ስለተረፍን ደግሞ ፈጣሪያችንን እናመሰግናለን" ብላለች።
እስካሁን በአደጋው 400 ሰዎች ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን ይህ ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ስጋት አለ። የአደጋ ጊዜ ሰራተኞችም በሕይወት የተረፈ ሰው ለማግኘት ፍለጋቸውን ቀጥለዋል።
አንዳንድ የቁፋሮ ማሽን አሽከርካሪዎች ለፋሲካ በዓል በመሄዳቸው በሕይወት የተረፉ ሰዎችን የማፈላለግ ሥራው አደጋ ላይ ነው።
ጊፍት ኦፍ ዘ ጊቨርስ የተባለ አንድ የእርዳታ ድርጅት የቁፋሮ ማሽኖች ላይ መሥራት ለሚችሉ ሰዎች ጥያቄ አቅርቧል።
ምናልባት ይህ ሊደርስ የሚችለው ሕይወትን ከመታደግ በተቃራኒ አስክሬኖችን ለማውጣት ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ አሁንም ነዋሪዎች በእጃቸው ፍርስራሹን እየቆፈሩ ነው።
ንጹህ የመጠጥ ውሃ ፍለጋም ሌላኛው ፈተና ሆኗል። ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በግዛቱ የተከሰተው ጎርፍ ቤቶችን አውድሟል፣ የኃይል መስመሮችን፣ መንገዶችን እና ድልድዮችን አፈራርሷል።
በሰሜን ደርባን በአማኦቲ ነዋሪዎች ከአንድ ከፈነዳ የቧንቧ መስመር ውሃ ለማግኘት ተሰባስበዋል።
የወረፋው ሰልፍ ረጅም በመሆኑ ነዋሪዎች ተስፋቸው ተሟጧል።
" ቤታችን ውስጥ ውሃ የለም። ምንም መሥራትም ሆነ መመገብ አንችልም። መታጠብ አንችልም። መንግሥት እንዲረዳን እንፈልጋለን" ሲል አንድ ነዋሪ ለቢቢሲ ተናግሯል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ወደ 300 የሚጠጉ ትምህርት ቤቶች እና የተወሰኑ የጤና ተቋማት ከጥቅም ውጭ ሆነዋል።
የተወሰኑ ማኅበረሰቦችም መንገዶች እና ድልድዮች በመፈራረሳቸው ከሌላው አካባቢ ጋር መገናኘት እንዳይችሉ ሆነዋል።
ፕሬዚደንት ሲሪል ራማፎሳ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ወደ ግዛቱ አምርተው የደረሰውን ጉዳት ተመልክተዋል።
ፕሬዚደንቱ በወቅቱ የጎርፍ አደጋው "በአስርተ ዓመታት ውስጥ አስከፊው ጉዳት" ሲሉ ገልጸውታል።

የፎቶው ባለመብት, BBC / CAMILLA MILLS
ግዛቱ የአደጋ አካባቢ መሆኑን ያወጁት ፕሬዚደንቱ መንግሥታቸው በጎርፉ የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት እና የተጎዱ ቤተሰቦችን ለመርዳት ወደ ኋላ እንደማይል ቃል ገብተዋል።
የአየር ሁኔታ ባለሙያዎች የአየር ንብረት ለውጥ እንደዚህ ያሉ አስከፊ ክስተቶች የበለጠ እንዲደጋገሙ አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለዋል።
በባለሙያዎቹ ሃሳብ ላይ ነዋሪዎችና ተቺዎች የሚስማሙ ቢሆንም በግዛቱ መሠረተ ልማቶች ተገቢው መንገድ ባለመሰራታቸው እና የውሃ ማፋሰሻ በአግባቡ ባለመሰራቱ መንግሥትን ወቅሰዋል።
ይሁን እንጂ መንግሥት እነዚህ ክሶችን ውድቅ አድርጓል።












