የአዲስ አበባ ሙስሊም ተማሪዎች ከትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ውጭ ሶላት እንዲያደርጉ ተፈቅዷል ተባለ

ሙስሊም ተማሪዎች

የፎቶው ባለመብት, Miidiyaa hawaasaa/Facebook

ታትሟል

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የከተማዋ ሙስሊም ተማሪዎች ከትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ውጪ የዙሁር ሶላት እንዲያደርጉ መፈቀዱን አስታወቀ።

በመዲናዋ የሚገኙ ሙስሊም ተማሪዎች እኩለ ቀን አካባቢ የሚደረገውን ዙሁር ስግደት ከትምህር ቤት ቅጥር ግቢ ውጪ እንዲያደርጉ የከተማው ትምህርት ቢሮ መፍቀዱን የምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዝደንት ሼክ አሊ መሐመድ ሺፋ ለቢቢሲ ገልጿል።

በጉዳዩ ላይ ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አስተያየት ለማካተት ያደረግነው ጥረት ስልክ ባለመነሳቱ አልተሳካም።

ባለፉት ቀናት ከዙሁር ሶላት ጋር በተያያዘ በሙስሊም ተማሪዎች እና በአንዳንድ ትምህር ቤቶች መካከል አለመግባባቶች ተከስተው ነበር።

ባለፈው ሳምንት የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ኡስታዝ መሐመድ አባታ፤ ሙስሊም ተማሪዎች የዙሁር ሶላት እንዳያደርጉ በትምህር ቤቶች ይከለከላሉ ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

"ትምህርት ቤት ውስጥ 'ሶላት እናድርግ' ሲሉ ይከለከላሉ። 'ውጪ ላይ ሶላት አድርገን እንመለስ' ሲሉም በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች ይከለከላሉ" በማለት ያለውን ሁኔታ ገልጸዋል።

የከተማዋ ሰላም እና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ከሃይማኖት ጋር ተያይዞ አየታዩ ላሉ የፀጥታ ስጋቶች ምላሽ ለመስጠት ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ እና ከአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አመራሮች ጋር ውይይት አካሂዶ ነበር።

መጋቢት29/2014 ዓ.ም በተካሄደው ውይይት "በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ ሃይማኖትን ተገን በመድረግ እየተፈጠሩ ያሉት የፀጥታ ችግሮችን ወጥነት ባለው መልኩ ለመፍታት ከትምህርት ማኅበረሰቡና ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እንደሚደረግ ተጠቁሟል" ሲል የከተማው ኮሚኒኬሽን ቢሮ ገልጾ ነበር።