ጃፓን የሩሲያ የድንጋይ ከሰል ወደ አገሯ እንዳይገባ አገደች

የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ ኪሺዳ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ ኪሺዳ ስምንት የሩሲያ ዲፕሎማቶችን ማባረሯንና ሙሉ በሙሉ ከሩሲያ የምታስገባውን የድንጋይ ከሰል ማገዷን አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት አርብ ዕለት በቶክዮ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።

"ሩሲያ ሰላማዊ ሰዎችን በመግደልና የኒዩክሌር ኃይል ማበልጸጊያ ላይ ጥቃት በመፈፀም በተደጋጋሚ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕጎችን ጥሳለች፤ ይህም ይቅር የማይባል የጦር ወንጀል ነው" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው።

ጃፓን ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ አገራት ጋር በመተባባር በሩሲያ ላይ ማዕቀብ መጣሏን ቀጥላለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኪሺዳ ጃፓን ከዩክሬን ጎን እንደምትቆምም ተናግረዋል።

ጃፓን የድንጋይ ከሰል ወደ አገሯ በማስገባት ከዓለም አገራት ሕንድና ቻይናን በመከተል በሦስተኛ ደረጃ ትገኛለች። ወደ አገሯ ከምታስገባው የድንጋይ ከሰል ውስጥም 11 በመቶ የሚሆነውን የምታስመጣው ከሩሲያ ነው።

በዚህ ሳምንት አሜሪካ የሩሲያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን ሴት ልጆች ላይ ጨምሮ በፕሬዚደንቱ የቅርብ ሰዎች ላይ ማዕቀብ መጣሏ ይታወቃል።

ማዕቀቡ ከተጣለባቸው ሌሎች ግለሰቦች እና ተቋማት መካከል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሴረጌ ላቭሮቭ ቤተሰቦች እና ዋና ዋና ባንኮች ይገኙበታል።

ዩናይትድ ኪንግደምም በስምንት የሩሲያ ባለሃብቶች እና የአገሪቷ ትልቅ የፋይናንስ ተቋማት ስበርባንክና 'ክሬዲት ባንክ ኦፍ ሞስኮ' ባንክ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ጥላለች።

በዩክሬን ውስጥ የጦር ወንጀሎች እየተፈፀመ ነው የሚለው ስጋት እየጨመረ በመምጣቱ የአውሮፓ ሕብረት ሩሲያ ወደ ውጭ የምትልከውን የድንጋይ ከሰል ለማገድ እየተወያየ መሆኑ ተገልጿል።

በሌላ በኩል የሩሲያ ቢሊየነር የግል አውሮፕላን በዩናይትድ ኪንግደም እንዳይበር ታግዷል።

ባለቤትነቱ የኡጌን ሺቪድለር የሆነው አውሮፕላኑ ለመብረር ፈቃድ የነበረው ሲሆን የተካሄደ ምርመራን ተከትሎ መታገዱ ተገልጿል።

መጋቢት ወር ላይ የዩኬ ትራንስፖርት ሴክሬታሪ ግራንት ሻፕስ አውሮፕላኑ ከደቡብ ምስራቅ ለንደን ከሚገኘው ቢጊን ሂል አውሮፕላን ማረፊያ እንዳይነሳ አግደዋል። ይህ የሆነው በአውሮፕላኑ ባለቤትነት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ለመፍቀድ ነበር።

አውሮፕላኑ ወደ ለንደን ያቀናው ጥገና ለማድረግ ነበር።

አውሮፕላኑን በአየር ማረፊያው ተገኝተው የጎበኙት ሻፕስ፤ "ከፑቲን አገዛዝ ተጠቃሚ የሆኑ የሩሲያ ባለሃብቶች ከዚህ ቀደም እንደነበረው ንግዳቸውን እንዲያካሂዱ አይፈቀድላቸውም ፤ አውሮፕላኑም የትም አይሄድም" ብለዋል።

ሻፕስ አክለውም "ሁሉም የሩሲያ አውሮፕላኖች በዩኬ ዕይታ ለመብረር ብቁ ያልሆኑ ተብለው ተመድበዋል፤ ምክንያቱም በተጣለው ማዕቀብ ሳቢያ በትክክል ጥገና እያገኙ አይደለም" ሲሉ ተናግረዋል።