ዩክሬን ጦርነት፡ አሜሪካ በፑቲን ሴት ልጆች ላይ ጨምሮ ተጨማሪ ማዕቀቦችን ጣለች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አሜሪካ የሩሲያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን ሴት ልጆች ላይ ጨምሮ በፕሬዚደንቱ የውስጥ ሰዎች ላይ ማዕቀብ ጣለች።
ማዕቀቡ ከተጣለባቸው ሌሎች ግለሰቦች እና ተቋማት መካከል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሴረጌ ላቭሮቭ ቤተሰቦች እና ዋና ዋና ባንኮች እንደሚገኙበት ዝርዝሩ ያሳያል።
እርምጃው የተወሰደው በዩክሬን ዋና ከተማ ኪዬቭ አቅራቢያ በምትገኘው ቡቻ ከተማ ጎዳናዎች ላይ የተጣሉት የሰላማዊ ሰዎች አስክሬኖች ምስሎችን ጨምሮ የሩሲያ ወታደሮች በዩክሬን ውስጥ የፈፀሙት አዲስ ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ይፋ መውጣቱን ተከትሎ ነው።
ሩሲያ ምስሎቹ ያለምንም ማስረጃ በኪዬቭ ባለሥልጣናት የተቀነባበሩ ናቸው ብሏል።
ምንም እንኳን የሳተላይት ምስሎች የሩሲያ ወታደሮች ቡቻ ከተማን ተቆጣጥረው በነበረበት ሰዓት ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ቢያሳዩም ፕሬዚደንት ፑቲን ረቡዕ ዕለት ድርጊቱን " በኪዬቭ አገዛዝ አሰቃቂውና አሳፋሪው ቅስቀሳ" ሲሉ የቀረበውን ክስ አጣጥለውታል።
የአሜሪካው ፕሬዚደንት ጆ ባይደን በበኩላቸው ረቡዕ ዕለት በቡቻ ተፈፀመ የተባለውን ግድያ በማንሳት የተፈፀመው ወንጀል " ከትላልቅ የጦር ወንጀሎች የሚተናነስ አይደለም።" ብለዋል።
በመሆኑም ኃላፊነት የሚሰማቸው አገራት እነዚህን ወንጀለኞች ተጠያቂ ለማድረግ መሰባሰብ አለባቸው" ሲሉ ባይደን አክለዋል።
አሜሪካ የፕሬዚደንት ፑቲን ሴት ልጆች ካትሪና ቭላድሚሮቭና ቲከሆኖቫ እና ማሪያ ቭላዲሚሮቭና ቮሮንሶቫ " ንብረታቸው እና ከንብረታቸው የሚያገኙት ጥቅም የታገደባቸው "የፑቲን አዋቂ ልጆች" በመሆናቸው እንደሆነ አስታውቃለች።
የማዕቀቡ ዝርዝር የወጣበት መግለጫ የፑቲን ሴት ልጅ ቲክሆኖቫ "የምትሰራው የሩሲያን መንግሥትና መከላከያ ሚኒስቴርን በሚደግፍ ተቋም የቴክኖሎጂ ሥራ አስፈፃሚ ሆና ነው" ይላል።
በተጨማሪም እህቷ ቮሮንሶቫ፣ ለዘረ መል የምርምር ሥራ ከክሬሚሊን ቢሊየን ዶላሮች ድጋፍ በተቀበለና ፑቲን በግላቸው የሚቆጣጠሩት በመንግሥት የሚደገፉ ፕሮግራሞችን እንደምትመራ ተገልጿል።
አሜሪካ ለምን የፕሬዚደንት ፑቲን ልጆችን ኢላማ እንዳደረገች ጥያቄ የቀረበላቸው የባይደን አስተዳደር ባለሥልጣን "ልጆቹ የተወሰኑ የአባታቸውን ንብረቶችን ሊያስተዳድሩ እንደሚችሉ በማሰብ ነው" ብለዋል።
" ፑቲንና አጋሮቻቸው እና ከፖለቲካ ጋር ግንኙነት ያላቸው ባለሃብቶች ንብረቶቻቸውንና ሃብታቸውን እንደደበቁ የምናምንበት ምክንያት አለን፤ ብዙዎቹ የፑቲን ንብረቶች፣ ንብረቶቻቸውን በአሜሪካ የፋይናንስ ሥርዓት እንዲሁም በሌሎች የዓለም አገራት ባስቀመጡ የቤተሰብ አባላት ተደብቀዋል ብለን እናምናለን። ለዚህም ነው ልጆቹን ኢላማ ያደረግነው" ብለዋል ባለሥልጣኑ።
ዋይት ሃውስ በሩሲያ ላይ የጣለው ማዕቀብ ኢላማዎች የትኞቹ ናቸው?
አሜሪካ በፑቲን ቤተሰቦች ላይ ጨምሮ በሌሎች የአገሪቷ ትላልቅ ተቋማት ላይ ማዕቀብ ጥላለች። እነዚህም፦
- ሩሲያ ውስጥ አዲስ ኢንቨስትመንት ለማገድ የተወሰደ ምጣኔ ሃብታዊ እርምጃ
- በሩሲያ ትልቁ የግል ባንክ አልፋ ባንክ እና በትልቁ የፋይናንስ ተቋም ስበርባንክ ላይ ከባድ የገንዘብ እቀባዎች
- ዋና ዋና የመንግሥት ኢንተርፕራይዞች ላይ እና
- በሩሲያ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና የቤተሰቦቻቸው አባላት ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች ናቸው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዩናይትድ ኪንግደም በስምንት የሩሲያ ባለሃብቶች እና የአገሪቷ ትልቅ የፋይናንስ ተቋማት ስበርባንክና 'ክሬዲት ባንክ ኦፍ ሞስኮ' ባንክ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ጥላለች።
በዩክሬን ውስጥ የጦር ወንጀሎች እየተፈፀመ ነው የሚለው ስጋት እየጨመረ በመምጣቱ የአውሮፓ ሕብረትም ሩሲያ ወደ ውጭ የምትልከውን የድንጋይ ከሰል ለማገድ እየተወያየ ነው።
አዲሱ ማዕቀብ በዋይት ሃውስ ይፋ ከመደረጉ ቀደም ብሎ የዩክሬኑ ፕሬዚደንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ " ምንም ዓይነት ለውሳኔ መፍረክረክን ልንታገስ አንችልም" ብለዋል።












