ተጨማሪ ዘጠኝ የኮቪድ-19 ምልክቶች ይፋ ሆኑ

አፍንጫዋን የምትጠርግ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ በኮሮናቫይረስ የተያዘ ሰው የሚያሳያቸው ምልክቶች ላይ ተጨማሪ ዘጠኝ ምልክቶች ተጨመሩ። እነዚህ ምልክቶች ከዚህ በፊት የነበሩትን የሚያሰፉና ተጨማሪ ነገሮችን ከግምት ውስጥ የሚያስገቡ ናቸው።

የዩኬ የጤና ደህንነት ኤጀንሲ ባዘጋጀው አዲስ መመሪያ ውስጥ የጉሮሮ ህመም፣ የጡንቻ ህመም እና 'ተቅማጥ' ከተካተቱት አዳዲስ የኮሮረናቫይረስ ምልክቶች መካከል ናቸው።

ይህ መመሪያ የወጣው ወረርሽኙ ከተከሰተ ሁለት ዓመታት ካለፈው በኋላ ሲሆን እንግሊዝ ውስጥ ደግሞ ይደረግ የነበረው የነጻ ምርመራ ከተቋረጠ ከቀናት በኋላ ነው።

ነገር ግን የዩኬ የጤና ደህንነት ኤጀንሲ ባስተላለፈው የማስጠንቀቂያ መልእክት አዳዲሶቹ ምልክቶች ከጉንፋን ብዙም ያልተለዩ መሆናቸውን አሳስቧል።

ከዚህ በፊት የሚታወቁት የኮቪድ-19 ምልክቶች ትኩሳት፣ የማያቆም ሳል፣ የሽታ እና የመቅመስ ስሜቶቻችን መጥፋት እንዲሁም ድካም የሚጠቀሱ ናቸው።

ወረርሽኙ ባጋጠመበት የመጀመሪያዎቹ ወራት ወቅት የስርጭቱን አካሄድ መረዳትና ምልክቶቹን መለየት ከባድ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ግን ዓለም ስለቫይረሱ ማወቅ ከሚገባው አብዛኛውን ነገር አውቋል። የዓለም ጤና ድርጅትም ቢሆን ከረጅም ጊዜ በፊት ምልክቶች ብሎ ያስቀመጣቸው ነገሮች በርካታ ናቸው።

ነገር ግን ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ትክክለኛ ምልክቶቹ የትኞቹ ናቸው እንዲሁም ምን አይነት ምልክቶችን የሚያሳይ ሰው ነው ምርመራ ማድረግ ያለበት የሚሉት ጥያቄዎች መከራከሪያ ሆነው ቆይተዋል።

ለምሳሌ ራስ ምታት የኮሮናቫይረስ ምልክት ተደርጎ ሊቆጠር የሚችል ቢሆንም ራሱን ያመመው ሰው በሙሉ ግን የኮሮናቫይረስ ምርመራ ማድረግ አይችልም። ምክንያቱም ራስ ምታት ከኮሮናቫይረስ ውጪ በበርካታ ምክንያቶች ሊከሰት ይችላል።

ትኩሳት፣ ሳል፣ ማሽተት ማቆም አልያም ጣእም ማጣት በርካቶችን የማያከራክሩ ምልክቶች ሲሆኑ አሁን ላይ ደግሞ ዘጠኝ ተጨማሪ ምልክቶች እንዲጨመሩ ተደርጓል።

እነዚህም ትንፋሽ ማጠር፣ ድካም፣ የሰውነት መላሸቅ፣ ራስ ምታት፣ የጉሮሮ ሕመም፣ ከአፍንጫ የሚወጣ ፈሳሽ [ንፍጥ]፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ ተቅማጥ እና አጠቃላይ የጤንነት ስሜት ማጣት ናቸው።

ዩኬ ውስጥ በኮቪድ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 4.9 ሚሊየን የደረሰ ሲሆን መንግስት በነጻ ሲያከናውነው የነበረው ምርመራም ባሳለፍነው ሳምንት ተጠናቋል።

የዩኬ የጤና ደህንነት ኤጀንሲ እንደሚለው ሰዎች አሁንም ቢሆን በተቻላቸው መጠን ከቤታቸው ላለመውጣት መሞከርና ከሌሎች ሰዎች ጋር ያላቸውንም ንክኪ መቀነስ አለባቸው። በተለይ ደግሞ እነዚህን ምልክቶች የሚያሳይ ሰው ምርመራ ማድረግና እራሱን ከሰዎች መለየት እንዳለበት ኤጀንሲው አሳስቧል።