በአፋር አብአላ በኩል የእርዳታ አቅርቦት ወደ ትግራይ ማጓጓዝ መጀመሩ ተነገረ

ታትሟል

በአፋር ክልል በኩል ወደ ትግራይ ክልል የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት በየብስ መጓጓዝ መጀመሩን የኢትዮጵያ መንግሥት አስታወቀ።

በአፋር በኩል ዋነኛው የእርዳታ አቅርቦት መስመር በሆነው የአብአላ መንገድ እርዳታ የጫኑ 21 ከባድ ተሽከርካሪዎች በዓለም ምግብ ድርጅት አማካኝነት ወደ ትግራይ ክልል ማጓጓዝ መጀመሩ ተገልጿል።

ይህም በጦርነቱ ምክንያት ለወራት ተቋርጦ የነበረው በየብስ የእርዳታ አቅርቦትን ወደ ትግራይ የማድረስ ተግባር የመጀመሪያ እርምጃ ነው።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው በትግራይ ክልል በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ዜጎችን ሕይወት ለመታደግ ሁሉንም አማራጮች በመጠቀም የሰብአዊ እርዳታን ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጿል።

ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል ሰብአዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች በተቀላጠፈ ሁኔታ እንዲደርስ ለማስቻል ግጭት ለማቆም መወሰኑን ማስታወቁ ይታወሳል።

በመንግሥት እንዳለው ለዚህ ውሳኔው ምክንያቱ በከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ሕይወት ለመታደግ እና እንግልትን ለመቀነስ "ከተለመደው የተለየ እርምጃን መውሰድ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ" ለሰብአዊነት ሲባል ግጭት የማቆም ውሳኔው ከሐሙስ መጋቢት 15/2014 ዓ. ም. ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚያደረግ ግለጾ ነበር።

መንግሥት ይህ ውሳኔ የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ "በትግራይ ክልል የሚገኙ አማጺያን ከማንኛውም ጥቃት እንዲታቀቡና በኃይል ከያዟቸው የአጎራባች ክልል አካባቢዎች እንዲወጡ" ጠይቋል።

ይህን ተከትሎም የህወሓት አመራሮች በሰጡት ምላሽ በበቂ መጠን እና ተቀባይነት ባለው ጊዜ ሰብዓዊ እርዳታ ወደ ትግራይ የሚደርስ ከሆነ ጥሪውን እንደሚቀበሉ ገልጸው፤ በክልሉ ካለው የሰብዓዊ እርዳታ ፍላጎት ጋር ተመጣጣኝ የሆነ እና ተቀባይነት ባለው ጊዜ የሰብዓዊ እርዳታው የሚደርስ ከሆነ "የትግራይ መንግሥት ግጭት ለማቆም ቁርጠኛ" መሆኑን አሳውቋል።

ነገር ግን ህወሓት ሰኞ መጋቢት 19/2014 ባወጣው መግለጫ፤ ግጭት ቆሞ የሰብዓዊ እርዳታ ለማቅረብ የተደረሰው ስምምነት ቀናት ቢያስቆጥርም ምንም አይነት የእርዳታ አቅርቦት ወደ ክልሉ እንዳልገባ አመልክቶ ነበር።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ማክሰኞ መጋቢት 20/2014 ዓ.ም. እንዳለው ደግሞ የፌደራሉ መንግሥት ወደ ትግራይ በየብስ እርዳታው ለማቅረብ ጥረት ቢያደርግም ህወሓት ሊተባበር ባለመቻሉ የእርዳታ አቅርቦት ሥራው እክል ገጥሞታል ብሏል።

ለዚህም የእርዳታ አቅርቦት መተላለፊያ የሆነው የአብኣላ መንገድ በህወሓት ታጣቂዎች በመዘጋቱ የዓለም የምግብ ፕሮግራም እንዲያጓጉዛቸው የተዘጋጁት 43 የጭነት ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ መግባት አለመቻላቸውን ገልጾ ነበር።

ነገር ግን ግጭት የማቆም ውሳኔው ይፋ ከሆነበት ዕለት ጀምሮ የመድኃኒት፣ የህክምና መሳሪያዎች፣ ገንዘብና አልሚ ምግቦችን ረጂ ድርጅቶች በቻሉት መጠን በአየር ትራንስፖርት በየዕለቱ እያጓጓዙ መሆናቸውን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አመልክቷል።

በ2013 ዓ. ም. ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተቀስቅሶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች በተስፋፋው ጦርነት ምክንያት ከፍ ያለ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት መድረሱ የተነገረ ሲሆን፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለችግር ተዳርገዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለው ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ በሰሜን ኢትዮጵያ የሰብአዊ እርዳታ የሚያስፈልገው ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን ገልጿል።

ጦርነቱ እስካሁን መቋጫ ስላላገኘ የተፈናቀሉትን ወደ ቀያቸው ለመመለስና እርዳታ ለማቅረብ አስቻጋሪ በመሆኑ በአስቸኳይ እርዳታ ማቅረብ ካልተቻለ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት አደጋ ላይ እንደሚወድቅ የእርዳታ ድርጅቶች ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል።

ህወሓት የኢትዮጵያ መንግሥት እርዳታ ወደ ትግራይ ክልል እንዳይገባ እገዳ ጥሏል በማለት ሲከስ፣ መንግሥት ደግሞ በእርዳታ አቅርቦት መስመሮች ላይ ጥቃት በመክፈት የእርዳታ አቅርቦትን ያስተጓጎለው አማጺው ኃይል ነው ሲል መቆየቱ ይታወቃል።