ሰሜን ኮርያ የተከለከለ አህጉር አቋራጭ ሚሳኤል ለሙከራ ተኮሰች

በቅርቡ የተተኮሰው ሚሳኤል ሰሜን ኮርያ ከአምስት ዓመታት በፊት ከተኮሰችው በተሻለ ጠንካራና ዘመነኛ ይመስላል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በቅርቡ የተተኮሰው ሚሳኤል ሰሜን ኮርያ ከአምስት ዓመታት በፊት ከተኮሰችው በተሻለ ጠንካራና ዘመነኛ ይመስላል።
ታትሟል

ሰሜን ኮሪያ ክልከላ የተጣለበት አህጉር አቋራጭ ሚሳኤል ለሙከራ መተኮሷን ደቡብ ኮርያ እና ጃፓን ይፋ አደረጉ።

የጃፓን ባለሥልጣናት ሚሳኤሉ 1,100 ኪሎ ሜትሮች የሚወነጨፍ ሊሆን እንደሚችል ገምተዋል።

ለሙከራ በሰሜን ኮሪያ ተተኮሰ የተባለው ይህ ሚሳኤል ለአንድ ሰዓት ከተጓዘ በኋላ በጃፓን ባሕር መውደቁ ተነግሯል።

ይህ አህጉር አቋራጭ ተወንጫፊ ሚሳኤል (አይሲቢኤም) ሺህ ኪሎ ሜትሮች መጓዝ የሚችል በመሆኑ አሜሪካ ሊደርስ እንደሚችል ይታመናል።

ሰሜን ኮርያ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ለሙከራ ሚሳኤሎች ስትተኩስ ነበር።

ፒዮንግያንግ የተተኮሱት ሳተላይቶች ናቸው ብትልም አሜሪካ እና ደቡብ ኮርያ እንደሚሉት የተተኮሰው አይሲቢኤም ነው።

በቅርቡ የተተኮሰው ሚሳኤል ሰሜን ኮርያ ከአምስት ዓመታት በፊት ከተኮሰችው በተሻለ ጠንካራና ዘመናዊ ይመስላል።

ይህ ሚሳኤል እስከ 6,000 ኪሎ ሜትር ከፍታ እንደሚወጣ የጃፓን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

ደቡብ ኮርያ በምላሹ አምስት ጊዜ ለሙከራ ሚሳኤሎች ከየብስ፣ ከባሕር እና ከአየር ተኩሳለች።

አሜሪካ እና ደቡብ ኮርያ ከሰሞኑ ሰሜን ኮርያ አይሲቢኤም ለሙከራ እንደምትተኩስ ሲያስጠነቅቁ ነበር።

ከአውሮፓውያኑ 2017 ወዲህ ይህ መሣሪያ በረዥም ርቀት ሲሞከር የመጀመሪያው ነው።

መጋቢት 16 ሰሜን ኮርያ የተኮሰችው ሚሳኤል ከፒዮንግያንግ ከተነሳ በኋላ እንደፈነዳ የደቡብ ኮርያ ወታደራዊ ኃይል አስታውቋል።

የደቡብ ኮርያ ፕሬዝዳንት ሙን ዣይኢን የሚሳኤል ሙከራውን አውግዘዋል።

"በአህጉር ተሻጋሪ ሚሳኤል ላይ የተጣለውን ክልከላ የጣሰ ነው። ኪም ጆንግ ኡን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይህንን ሚሳኤል ላለመተኮር ቃል ገብተው ነበር" ሲሉ ወቅሰዋል።

ሚሳኤሉ መተኮሱ የተባበሩት መንግሥታትን ስምምነት እንደሚጥስ ፕሬዝዳንቱ አያይዘው ገልጸዋል።

ተንታኞች እንደሚሉት ኪም ጆንግ ኡን ደቡብ ኮርያ ወታደራዊ ጥቃት ይደርስብኛል በሚል ስጋት ውስጥ እንድትኖር ነው የሚሹት።

አሜሪካ አጋሮቿን ለመርዳት እንዳትችል በሚል የኒውክሌር ጥቃታቸው አሜሪካ እንዲደርስም ይፈልጋሉ።

ሰሜን ኮርያ ሩስያ ዩክሬንን በወረረችበት መጠን አስጊ ላትሆን ትችላለች።

ነገር ግን እስያ ውስጥ ያለውን የደኅንነት መዋቅር መዘወር ትፈልጋለች።

አሜሪካ እና አገር አገሮቿ ቻይና እና ሩሲያን ጨምሮ የሰሜን ኮርያን የመሣሪያ ክምችት የሚያዳብሩ አገራት ላይ ማዕቀብ እንዲጣል በተባበሩት መንግሥታት ጫና ማሳደር እንደሚኖርባቸው ይታመናል።

የተባበሩት መንግሥታት ሰሜን ኮርያ ባለስቲክ ሚሳኤል እና ኒውክሌር እንዳትሞከር እገዳ ጥሏል።

እአአ በ2018 ኪም ጆንግ ኡን ከቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ንግግር ካደረጉ በኋላ ረዥም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤል ሙከራን ለተወሰነ ጊዜ ለማቆም ወስነው ነበር።

ነገር ግን በ2020 ቃላቸውን ለማጠፍ መወሰናቸውን ይፋ አድርገዋል።

በ2017 ሰሜን ኮርያ ሀዋሶንግ 12 የሚባል አይሲቢኤም 4,500 ኪሎ ሜትር ከፍታ የሚወጣ ሚሳኤል ሞክራለች።

አሁን የተኮሰችው ሀዋሶንግ 14 ከፍተኛ ኃይል ያለውና 8,000 ኪሎ ሜትር የሚወጣ ነው።