ኔቶ ተጨማሪ ወታደሮችን ወደ ምሥራቅ አውሮፓ ሊልክ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት [ኔቶ] ወደ ምሥራቅ አውሮፓ ተጨማሪ ወታደሮችን የማሰማራትን ሀሳብ ሊያጸድቅ እንደሆነ ዋና ፀሐፊው የንስ ስቶልተንበርግ ተናገሩ።
ዋና ፀሐፊው ዩክሬን ላይ በሩሲያ የተፈጸመመውን ወረራ በተመለከተ ሊካሄድ ከታሳበው አስቸኳይ ስብሰባ አንድ ቀን ቀደም ብለው ነው ይህንን ያሉት።
ለሀንጋሪ፣ ስሎቫኪያ፣ ቡልጋሪያ እና ሩሜኒያ ተጨማሪ ወታደሮች እንደሚላኩ ተናግረዋል።
ከዚህ ባሻገርም ኔቶ ለዩክሬን ከፍ ያለ ድጋፍ ለማደረግ እንዲሁም ዩክሬንን ከኬሚካል፣ ከባዮሎጂካል እና ከኒውክለር ጦር መሳሪያዎች ለመጠበቅ ታስቧል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በዚህ አስቸኳይ ስበሰባ ላይ ለመገኘት እና ከአውሮፓ አገራት መሪዎች ጋር ለመገናኘት ወደ ብራሰልስ እየተጓዙ ነው።
ፕሬዝዳንቱ በአውሮፓ በሚኖራቸው ቆይታ አስተዳደራቸው በሩሲያ ላይ ተጨማሪ ጠበቅ ያሉ ማዕቀቦችን እንደሚያስተላልፍ ይጠበቃል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ለፈረንሳይ የሕዝብ እንደራሴዎች ባደረጉት ንግግር የፈረንሳይ ኩባንያዎች ሩሲያን ለቅቀው እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
በሌላ በኩል እስራኤል ለዩክሬን ልትሸጠ የነበረውን 'ፔጋሰስ' የተሰኘ የስለላ ሶፍትዌር ለጊዜው ማገዷን ገልጻለች። ምክንያቱ ደግሞ ምናልባት ይህ ውሳኔ ሩሲያን ሊያስቆጣት ይችላል በሚል ስጋት ነው።
የኔቶ ዋና ፀሐፊ በንግግራቸው የድርጅቱን አጠቃላይ ወታደራዊ ቁመና ማሻሻል ተገቢ እንደሆነ በመጠቆም ከዚህ በኋላ በምድር፣ በአየር እንዲሁም በባሕር ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች መጠናከር እንዳለባቸው አባል አገራት ይስማማሉ ብለዋል።
በአጠቃላይ ኔቶ በምሥራቃዊ አውሮፓ ድንበር በኩል 40 ሺህ የሚደርሱ ወታደሮች ያሉት ሲሆን ይህም ከባልቲክ ክልል እስከ ጥቁር ባሕር የሚደርስ ነው።
ዋና ፀሐፊው አክለውም ማንኛውም አይነት ባዮሎጂካልም ሆነ የኬሚካል ጦር መሳሪያዎችን መጠቀም ከባድ መዘዝ ይዞ እንደሚመጣ በማሳሰብ ኔቶ አባል አገራቱን እና ወዳጆቹን ከማንኛውም አይነት ጥቃት ለመከላከል ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ዋሽንግተን መረጃዎችን በአግባቡ ከመረመረች በኋላ ሩሲያ ዩክሬን ውስጥ የጦር ወንጀል መፈጸሟን አረጋግጠናል ብለዋል።
ባሳለፍነው ሳምንትፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የሩሲያውን ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን 'የጦር ወንጀለኛ' ማለታቸው የሚታወስ ነው።
ሞስኮ ኒው ዮርክ ከሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ዲፕሎማቶቿ ከተባረሩ በኋላ በምላሹ ከአገሯ የምታባርራቸውን የአሜሪካ ዲፕሎማቶች ስም ዝርዝር ለዋሽንግተን ልካለች።
በተያያዘ ዜና ፖላንድ 45 የሚሆኑ የሩሲያ ዲፕሎማቶች ከአገሯ እንዲወጡ ልታደርግ መሆኑን ያስታወቀች ሲሆን ከእነዚህ መካከል ግማሽ ያክሉ ዋርሶ ውስጥ በሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ የሚሰሩ ናቸው።












