ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሕሙማን እና አረጋውያን ያለተጨማሪ ህመም እና ስቃይ እንዲኖሩ የሚጥረው 'ግሬስ'
ዊንታ ተስፋዬ የአባቷ እህት ታማሚ በመሆናቸው ተጎድተው እንደነበር ታስታውሳለች።
የቤተሰቡ አባላት የዕለት ኑሮውን ለማሸነፍ በየፊናው ሲሮጥ ስለሚውል፣ እንክብካቤ ይደረግላቸው የነበረው የቤት ሥራ እንድትሰራ በቀጠሯት ሠራተኛ ነበር።
ይህም ሆኖ ግን ልባቸውን የሚያሳርፍ ነገር ባለማግኘታቸው፣ አንዳንዴ ቤት ከእርሳቸው ጋር አርፍደው እንደሚወጡ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ በምሳ ሰዓት ወደ ቤት መጥተው ደኅንነታቸውን እንደሚያረጋግጡ ታስታውሳለች።
ይህ ግን በሥራቸውም ላይ ሆነ በሕይወታቸው ላይ ጫና ማድረሱ አልቀረም።
አክስቷ ምንም እንኳ ታማሚ ቢሆኑም እጅግ በጣም ጠንካራ በመሆናቸው አንስቶ ለማጣጠብ፣ ምግብ ለማብላት እና ሌሎች እንክብካቤዎችን ለማድረግ ተጨማሪ ድጋፍ ያስፈልግ አንደነበርም ጨምራ ገልፃለች።
"በዳይፐር ነው የነበረቸው" የምትለው ዊንታ፣ ተንከባካቢያቸው ንጽህናቸውን ለመጠበቅ፣ ሰዓት ጠብቆ ለማብላት እንዲሁም አካላቸውን እንዲያፍታቱ ለማንቀሳቀስ እንደምትቸገር ታስታውሳለች።
"በጣም ተጎድታ ነበር፣ ምግብ እምቢ ትለን ነበር፤ ጉሉኮሷ ወርዶ ነበር፤ አሟት ስለነበር ፈሳሽ መውሰድ ላይ ታስቸግረን ነበር።"
አክስቷ ታማሚ ስለሆኑ እና ረዥም ሰዓት ተኝተው ያሳልፉ ስለነበር ገላቸው ለስለት ተዳርጎ ነበር።
"በቤት ውስጥ እጥፍጥፍ ብላ ከመቀመጧ የተነሳ ሰውነቷ ተሳስሮ ነበር" የምትለው ዊንታ፣ የዘወትር የቤተሰቡ ስጋት የነበረው በዚህ ዓይነት ሁኔታ ከቀጠሉ ሊሞቱ ይችላሉ የሚል ነበር።
በዚህ ወቅት ነው ከመኖሪያ ቤታቸው በቅርብ ርቀት የተሟላ እንክብካቤ የሚሰጥ ማዕከል መከፈቱን የሰማችው።
ልክ እንደ እርሷ ሁሉ ባጋጠማቸው የጤና መታወክ ምክንያት የቀዶ ሕክምና የተደረገላቸው አቶ የሱፈንታ ብስራት ወደ ዚህ ማዕከል የመጡት የቅርብ ሕክምና ድጋፍና ክትትል ስለሚያስፈልጋቸው ነበር።
ግሬስ የህሙማን እና የአረጋውያን እንክብካቤ ማዕከል ቤተሰብ ከዕለት ተዕለት ተግባሩ ሳይሰናከል፣ ታማሚውም አስፈላጊው ክትትል እና እንክብካቤ ሳይጓደልበት አገልግሎት የሚሰጥ ነው።
ለሕሙማን እና ለአረጋውያን የሚሰጥ አገልግሎት
ዘመድ ወዳጅ ለትንሽ ለትልቁ አለሁ በሚልበት፣ የመረዳዳት እና የመተጋጋዝ ባህሉ ጠንካራ በሆነበት ኢትዮጵያ የቤተሰብ አባል ስለታመመ ወይንም እርጅና ስለተጫነው ብቻ ወደ ማዕከል ማስገባት የሚታሰብ አይመስልም።
ሕይወት በየአቅጣጫው ለሚያባትለው ሰርቶ በሌ ከተሜ ግን የሕሙማን እና የአረጋውያን እንክብካቤ ማዕከል መኖሩ እፎይታ የፈጠረ ይመስላል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የማዕከሉ ተጠቃሚዎችም ለእነርሱም ሆነ ለእንክብካቤ ፈላጊዎቹ "እፎይታን የሰጠ" አገልግሎት መሆኑን ይመሰክራሉ።
በግሬስ የህሙማን እና የአረጋውያን እንክብካቤ ማዕከል ውስጥ ሕክምና እና እንክብካቤ በጥምረት እንደሚሰጥ የሚናገሩት የማዕከሉ መስራች ዶ/ር ጽዮን ሠለሞን ናቸው።
ማዕከሉን ከጓደኛቸው ጋር በመሆን መመስረታቸውንም ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ባደረጉበት ወቅት ተናግረዋል።
ግሬስ 'ነርሲንግ ሆምን' ለማቋቋም ስለወሰኑባቸው ምክንያቶች ሲናገሩም ቀዳሚው የኮቪድ ወረርሽኝ ነው።
በወረርሽኙ ወቅት ህሙማን ከቤታቸው ወጥተው ወደ ሕክምና ተቋም ለመምጣት በመፍራታቸው የሕክምና ባለሙያዎች ታካሚዎቻቸውን ለማግኘት ተቸግረው እንደነበር ያስታውሳሉ።
ሌላው ምክንያታቸው ደግሞ ይሰሩበት የነበረው ሆስፒታል ውስጥ የቤተሰባቸው አባላት የታመሙባቸው ሰዎች አስታማሚ ተቸግረው፣ ሥራ እና የቤተሰብ ሕይወትን ማጣጣም ተስኗቸው መመልከታቸው ነው።
በተለይ የቤተሰብ አባላቶቻቸው ከአገር ውጪ የሚገኙ እና በአገር ውስጥ ያሉ ቤተሰቦቻቸው ሲታመሙ ክትትል የሚያደርግ፣ አቅፎ ደግፎ የሚያስታምም፣ ቀና አድርጎ ውሃ የሚያጠጣ ሰው አጥተው ሲቸገሩ ሲመለከቱ የእንክብካቤ ማዕከል መኖር አለበት ሲሉ አሰቡ።
ከዚህ ሁሉ ባሻገር ግን ገፊ ምክንያት የሆናቸው የጓደኛቸው አባት መታመም መሆኑን ያስታውሳሉ።
"አባቱን ለብቻው ሲያስታምም፣ ወጥቶ ሥራውን መስራት ሲቸገር ተመልክቻለሁ" የሚሉት ዶ/ር ጽዮን ይህ ደግሞ የሕክምና ወጪውን ለመክፈል በገንዘብ ረገድ መፈተኑ እንዳልቀረ ይናገራሉ።
እነዚህ ምክንያቶች ተደራርበው የእንክብካቤ እና የድጋፍ አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ የሚሰጥ ማዕከል ከጓደኛቸው ጋር ለመክፈት ወሰኑ።
በግሬስ የእንክብካቤ ማዕከል ውስጥ በእድሜ መግፋት የተነሳ ድጋፍ የሚያሻቸው፣ እንዲሁም የሕክምና ባለሙያ የቅርብ ክትትል የሚፈልጉ ሰዎች እንደሚመጡም ጨምረው ተናግረዋል።
ወላጆች ልጆቻቸውን አሳድገው ለወግ ማዕረግ ካበቁ በኋላ እነርሱን ደግሞ እስከ መጨረሻ ሕይወት ዘመናቸው ድረስ ተገቢውን እንክብካቤ እንዲያገኙ እንደሚሰሩም ይናገራሉ።
ማዕከሉ የገጠመው ተግዳሮቶች
የኢትዮጵያውያን አኗኗር እርስ በእርስ በመደጋገፍ ላይ የተመሰረተ መሆኑ ለማዕከሉ ተግዳሮት ሆኖበት እንደነበር ዶ/ር ጽዮን ያስታውሳሉ።
የታመሙ ሰዎችን እንክብካቤ ለመስጠት ከተቻለ የቤተሰብ አባል ካልሆነ ደግሞ ረዳት ተቀጥሮ የተቻለውን ሁሉ እንደሚያደረግ ይገልጻሉ።
ካልሆነ ለጎረቤት በአደራ ተትቶ የዕለት ጉዳይን ከውኖ መምጣትም የተለመደ ነው።
"በማዕከሉ እንክብካቤው ብቻ ሳይሆን ሕክምናውም አለ" የሚሉት ዶ/ር ጽዮን፣ ይህ በቤተዘመድ ከሚደረግ እንክብካቤ ይለያል ይላሉ።
ከዚህ ባሻገር ደግሞ እንክብካቤ ያስፈልገኛል ብሎ ወደ እነርሱ የሚመጣ ግለሰብ የአመጋገብ ሥርዓቱን በጠበቀ እና በባለሙያ የተዘጋጀ ምግብ እንዲመገብ እደሚያደርጉ ጨምረው ገልፀዋል።
የቤተሰብ ሸክምን ለመካፈል እንክብካቤ የሚፈልጉትም ያለ ተጨማሪ ህመም እና ስቃይ እንዲኖሩ ለማድረግ አስበው እንደሚሰሩም ያስረዳሉ።
"የእርስ በእርስ መረዳዳታችንን ዘመናዊ በሆነ መልኩ አንድ እርምጃ ወደፊት ለማድረግ ሞክሬያለሁ" የሚሉት ዶ/ር ጽዮን፣ ሕሙማኑ ወደ ማዕከላቸው ሲመጡ ከኮቪድ ነጻ መሆን እንደሚረጋገጥ ገልፀዋል።
ከሆስፒታል የሚመጡ ደግሞ ሙሉ የሕክምና ታሪካቸውን፣ በተጨማሪም ከኮቪድ ነጻ መሆናቸውን የሚያሳይ ወረቀት እንዲያመጡ ይደረጋል።
በተቋሙ እርሳቸውን ጨምሮ ሦስት ዶክተሮችን እና ስድስት ነርሶች እንደሚሰሩ የሚናገሩት ዶ/ር ጽዮን "ያው ቀስ እያለ ብዙ ተመሳሳይ ነርሲንግ ሆም ይከፈታል ብዬ አስባለሁ" ይላሉ።
ዶ/ር ጽዮን እንዲህ ዓይነት ማዕከሉን በመላው ኢትዮጵያ፣ እንዲሁም በምሥራቅ አፍሪካ ደረጃ ተደራሽ ለማድረግ ህልም እንዳላቸው ጨምረው ገልፀዋል።
ዊንታ በግሬስ የእንክብካቤ ማዕከል ከሦስት ወር በላይ የሆናቸው አክስቷ፣ አሁን የጤናቸው ሁኔታ እየተሻሻለ መምጣቱን ትናገራለች።
"ከጤናዋ አንጻር ትክክለኛውን ውሳኔ ነው የወሰን ነው" በማለት ስላላቸው ለውጥ ስትናገር፣ "አሁን መራመድም እየሞከረች ነው፤ የአመጋገብ ሁኔዋም ተሻሽሏል" በማለት ከዚህ ከነበሩበት በተሻለ ሁኔታ ላይ እንደሆኑ ለቢቢሲ ገልጻለች።
አቶ የሱፈንታ በበኩላቸው "የቤተሰብ ያህል" እንክብካቤ ማግኘታቸውን ይናገራሉ።