እስራኤል ኢትዮጵያውያን ጎብኚዎች ለትንሳኤ በዓል ወደ አገሯ እንዳይገቡ እገዳ ጣለች

ታትሟል

እስራኤል ለትንሳኤ በዓል ኢትዮጵያውያን ክርስቲያን ምዕመናን ወደ አገሯ እንዳይገቡ ክልከላ መጣሏን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ቢገልጹም የኢትዮጵያ መንግሥት ውሳኔውን በተመለከተ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ገለጸ።

ከእስራኤል የሕዝብ እና ኢሚግሬሽን ባለሥልጣን በአገሪቱ ላሉ የቱሪስት ድርጅቶች በተላለፈው ትዕዛዝ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ጦርነት ምክንያት እገዳው መጣሉ ተገልጿል።

ባለሥልጣኑ ለዚህ ውሳኔው እንደምክንያት ያስቀመጠው ለጉብኝት ወደ እስራኤል የሚጓዙ ሰዎች ጦርነቱን ለመሸሽ ሲሉ ወደ አገራቸው ላይመለሱ ይችላሉ በሚል ስጋት መሆኑ ተዘግቧል።

ነገር ግን የኢሚግሬሽን ባለሥልጣኑ ባሰራጨው ደብዳቤ ላይ ለመጪው የትንሳኤ በዓል ወደ እስራኤል ለመጓዝ የሚፈልጉ ሰዎች ፈቃድ ለማግኘት ማመልከቻቸውን በተናጠል መቅረብ ይችላሉ ብሏል።

ይህን የባለሥልጣኑን ውሳኔ በእስራኤል ካሉ የጉብኝት ድርጅቶች በኩል እርምጃው ኢትዮጵያውያንን የሚመለከት በመሆኑ "ከፍ ያለ አድልዎ" የሚንጸባረቅበት መሆኑን በመግለጽ ተቃውመውታል።

ቢቢሲ ወደ እስራኤል የሚደረጉ ጉብኝቶችን ከእስራኤላውያን ድርጅቶች ጋር በጋራ የሚያስተባብሩ ኢትዮጵያውያን የአስጎብኚ ድርጅቶችን ጠይቆ እንደተረዳው ደብዳቤው እንደደረሳቸው አጋሮቻቸው አሳውቀዋቸዋል።

ይህንንም ተከትሎ ከእስራኤል የሕዝብ እና ኢሚግሬሽን ባለሥልጣን ያስተላለፈው ኢትዮጵያውያን ጎብኚዎችን የማገድ ውሳኔን መለስ ብሎ እንዲመረምርና ማስተካከያ እንዲያደርግ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በቡድን የመጡ በርካታ ቱሪስቶች "በሕገወጥ መንገድ" እዚያው መቅረታቸውን በመጥቀስ፣ ያለው ጦርነት ደግሞ ይህንን ሊያባብስ ይችላል በማለት እስራኤላውያን ባለሥልጣናት የወሰዱትን ይህንን እርምጃ ተከላክለዋል።

ጉዳዩን በተመለከተ የተጠየቁት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እስራኤል ስላሳለፈችው ውሳኔ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በየዓመቱ ለገና፣ ለጥምቀት እና ከትንሳኤ በዓል ጋር የተያያዙ ሃይማኖታዊ በዓላትን ለማክበር በርካታ ሰዎች በአስጎብኚ ድርጅቶች አማካይነት ወደ እስራኤል ጉዞ ያደርጋሉ።

ይህ የእስራኤል ውሳኔ የማይቀየር ከሆነ የበርካታ ሰዎች ሃይማኖታዊ ጉዞዎች የሚስተጓጎል ከመሆኑ በተጨማሪ ጉዞውን የሚያስተባብሩት የጉብኝት ድርጅቶች ኪሳራ እንደሚገጥማቸው ተናግረዋል።

አንድ ዓመት ተኩል ሊሆነው የተቃረበው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በርካታ የውጭ አገር ቱሪስቶችን በመሳብ የሚታወቁትን የሰሜን ኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻዎችን ከሥራ ውጪ በማድረጉ የጉብኝት ድርጅቶችና አገሪቱ ከፍተኛ ገቢ እንዳጡ ይታመናል።

በዚህ ላይ ወደ እስራኤል የሚደረጉ ጉብኝቶችን ከእስራኤል አስጎብኚዎች ጋር ለሚያዘጋጁት የኢትዮጵያ አስጎብኚዎች ይህ የእስራኤል እገዳ እንደሚጎዳቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አንድ አስጎብኚ እንደገለጸው ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በነበሩ የእንቅስቃሴ ገደቦች ምክንያት ከባድ ኪሳራ ለደረሰበት ድርጅቱ የእስራኤል እገዳ መጥፎ ዜና ነው ብሏል።