ጋናዊው ባለሀብት ቼልሲን በ3.1 ቢሊዮን ዶላር ሊገዙ እንደሆነ ተዘገበ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጋናዊው የንግድ ሰው የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ኃያል ክለብ የሆነውን ቼልሲ የእግር ኳስ ቡድንን በ3.1 ቢሊዮን ዶላር ለመግዛት ፍላጎታቸውን መግለጻቸው ተዘገበ።
በስፋት ዉንቱሚ በሚለው ቅጽል ስማቸው የሚታወቁት ጋናዊው ባለሀብት ቤርናርድ አንትዊ ቦሲያኮ የቼልሲ ቡድንን የመግዛት ፍላጎታቸው የሚሳካ ከሆነ የፕሪሚዬር ሊግ ኃያል ቡድን ባለቤት በመሆን የመጀመሪያው አፍሪካዊ ይሆናሉ።
ጋናዊው ባለሀብት ቡድኑን በእጃቸው ካስገቡ የማንችስተር ዩናይትዱን ክሪስቲያኖ ሮናልዶን እና የፓሪ ሴንጄርሜኑን ሊዮኔል ሜሲን የመሳሳሉ የእግር ኳስ ከዋክብትን ወደ ቡድኑ የማምጣት ፍላጉት እንዳላቸው ተነግሯል።
ጋናዊው ባለሀብት ቤርናርድ በአገሪቱ የወርቅ ማዕድን ማውጫ ባለቤት እና ፖለቲከኛ ሲሆኑ፣ በስፖርቱ ዘርፍ ብዙም የሚታወቅ ታሪክ ስለሌላቸው ቼልሲን የመግዛት ፍላጎታቸው ይፋ ሲሆን በርካታ ጋናውያንን አስደንቋል።
የግለሰቡ የሀብት ምንጭ የወርቅ ማዕድን ሲሆን በተጨማሪም የሬዲዮ እና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች አሏቸው። ነገር ግን አስካሁን ያላቸውን የሀብት መጠን በይፋ ገልጸው ስለማያውቁ ምን ያህል እንደሆነ መረጃ የለም።
ባለሀብቱ ቤርናርድ ከማዕድን ማውጣቱ በተጨማሪ በጋና ፖለቲካ ውስጥ ተሳታፊ ሲሆኑ፣ በዚህም የአገሪቱ ገዢ ፓርቲ የአሻንቲ ክልል ሊቀመንበር ናቸው።
የወቅቱ የቼልሲ እግር ኳስ ቡድን ባለቤት ሩሲያዊው ሮማን አብራሞቪች ሩሲያ ዩክሬንን መውረሯን ተከተሎ ባጋጠማቸው ጫና ቡድኑን እንደሚሸጡ ከሳምንት በፊት ማሳወቃቸው ይታወሳል።
አብራሞቪች የሩሲያው መሪ ቭላድሚር ፑቲን ጋር የቀረበ ግንኙነት አላቸው ከተባሉ ሩሲያውያን ከበርቴዎች መካከል አንዱ በመሆናቸው ከዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት በኩል እቀባዎች ተጥሎባቸዋል።
አብራሞቪች ቼልሲን ለመሸጥ ያላቸውን ፍላጎት ይፋ ካደረጉ በኋላ የጋናዊው ባለሀብት ጠበቆች እና የንግድ አማካሪዎች ከቼልሲ ባለቤት ጋር ድርድር ለማድረግ ለንደን እንደነበሩ ተገልጿል።
ከበርቴው ንብረታቸው በመታገዱ እና የጉዞ እቀባ ስለተጣለባቸው የእግር ኳስ ቡድናቸውን የመሸጥ ፍላጎታቸው ለጊዜው ተግባራዊ እንዳያደርጉ መገደዳቸው አይቀርም ተብሏል።
















