የትኞቹ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በሩሲያ ያላቸውን ስራ አቋረጡ?

የነዳጅ መርከቦች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ሰላሳ ዓመት ወደኋላ! ከሰላሳ ዓመታት በፊት በሶቭየት ኅብረት ኮምዩኒዝም ሲንኮታኮትና የሩሲያ በሮች ለኢንቨስትመንት እና ንግድ ሲከፈቱ ይህንን ዕድል ለመጠቀም የምዕራባውያን ኩባንያዎችን የቀደመ አልነበረም።

ያኔ እንደ ኮካ ኮላ እና ማክዶናልድስ ያሉ ታዋቂ ኩባንያዎች በሩሲያ ስራ ሲጀምሮ የሩሲያ አዲሱ ጊዜ መጣ እስከመባል ደርሶ ነበር። የተለያዩ ምርት አቅራቢዎች፣ ማዕድን አውጪዎች፣ የህግ አማካሪዎችና በርካታ ድርጅቶች ቀስ በቀስ በሩሲያ ተስፋፉ። ሩሲያውያንም በሌዊ ጂንስ መዘነጥ እና የምዕራብያውያኑ ቅንጡ ምርቶችን መጠቀም ጀመሩ።

ያ በር ከተከፈተ ሰላሳ ዓመታት ተቆጠረ። ከዚህ ሁሉ ዓመት በኋላ አዲስ ነገር ተፈጠረ። ሩሲያ ዩክሬንን ወረረች። ይህንንም ተከትሎ በርካታ የምዕራባውያኑ ክባንያዎች በሩሲያ ያለውን ስራቸውን እያቆረጡ ነው። አፕል፣ ላንድ ሮቨር፣ ኤች ኤንድ ኤም እና ቡርቤሪን ጨምሮ በርካታ ኩባንያዎች በሩሲያ ያላቸውን የንግድ እንቅስቃሴ ማቋረጣቸውን አስታውቀዋል።

ለመሆኑ የትኞቹ ኩብንያዎች ስራቸውን እያቆሙ ነው? ሌሎቹስ ለምን ዝምታን መረጡ?

የነዳጅ ኩባንያዎች

ቢፒ የተባለው በነዳጅ ዘርፍ የሚሰራ ኩባንያ በዩክሬን ግጭት እንደተቀቀሰ ነበር በሩሲያ ያለውን ስራ እንዲያቆም ጫና የተደረገበት።ኩባንያው በሩሲያው ግዙፉ የነዳጅ አምራችና አቅራቢ ኩባንያ ሮስኔፍት ውስጥ ትልቅ ድርሻ ቢኖረውም በቀናት ውስጥ ስራው እንደሚቋረጥ አስታውቋል።

ሼል፣ኤክሶንሞቢል እና ኢኩዊኖር የተሰኙት በነዳጅ ዘርፍ የሚሰሩ ኩባንያዎችም ከባለአክሲዮኖች፣ ከመንግሥታት እና ከዜጎች በደረሰባቸው ግፊት በሩስያ ያላቸውን ኢንቨስትመንቶችን እናቆማለን ብለዋል።

እነዚያ የነዳጅ አምራች እና አቅራቢ ኩባንያዎች ቀላል ዋጋ የሚሰጣቸው አይደሉም። የቢፒ የቅርብ ጊዜ ትርፉ በዘርፉ በአምስተኛ ደረጃ እንዲቀመጥ አድርጎታል። ሼል ከሩሲያው ግዝዙፍ የነዳጅ ተቋም ጋዝፕሮም ጋር ያለውን ግንኙነት ለማቋረጥ እስከ 3 ቢሊዮን ዶላር ሊከስር እንደሚችል ተገምቷል።

በሌላ በኩል ቶታል ኢነርጂ በሩሲያ ውስጥ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በገንዘብ እንደማይደግፍ ተናግሯል። ነገር ግን ከተወዳዳሪዎቹ በተጻራሪ ከነባር ኢንቨስትመንቶቹ የመውጣት እቅድ የለውም።

የዲዝኒ ካርቱን

የፎቶው ባለመብት, Disney

የመዝናኛ ዘርፍ

የዋርነር ብሮስን አዲሱ 'ብሎክበስተር ዘ ባትማን' በሩሲያ እንደማይታይ ተረጋግጧል። ይህ በሀገሪቱ ለሚገኙ የፊልም አፍቃሪዎች መልካም ዜና አይመስልም። ፊልም አምራች ኩባንያው በዚሁ በሰሞነኛ ጉዳይ ምክንያት በሀገሪቱ ውስጥ አዳዲስ ፊልሞችን ላለመልቀቅ ወስኗል።

ኔትፍሊክስ በሀገሪቱ ውስጥ ያሉትን ሁሉንም "ቀጣይ ፕሮጀክቶችን" ማገዱን ያስታወቀ ሲሆን " ወቅታዊ ሁኔታዎችን ተፅእኖ" እየገመገመገምኩ ነው ብሏል።

ሁሉም ኩባንያዎች ከውሳኔ ላይ የደረሱት ሩሲያ ላይ በተጣሉ ማዕቀቦች ምክንያት አላደረጉም። ይልቅስ ለውሳኔያቸው መነሻ ያደረጉት በዩክሬን ባለው "ሰብአዊ ቀውስ" ነው።

ነገር ግን ውሳኔው ለሩሲያ የሚያስተላልፈው ሌላ መልእክት ነው። ይህ መሆኑ የሩሲያውያንን የመገለል እንደሚጨምር ተገምቷል።

የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች

አፕል በሩሲያ ውስጥ ሁሉንም የምርት ሽያጭ ያቆመ ሲሆን እንደ ፔይ እና አፕል ማፕ ካርታ ያሉ ሌሎች አገልግሎቶችን ላይ ገደብ አድርጓል። በተጨማሪም በሀገሪቱ የሚገኙ የሽያጭ ሱቆቹን ተዘግተዋል።

በሞስኮ ላለፉት 24 ዓመታት ለሰራው አፕል ውሳኔው ራሱንም የሚጎዳው እንደሆነ ይታመናል።

በሌላ በኩል አንዳንድ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ከሃሰት መረጃ ጋር በተያያዘ በሩሲያ የሚገኙ አገልግሎቶች እየተገደበባቸው ነው።

ለምሳሌ ፌስቡክ በመንግሥት ቁጥጥር ስር ያሉ የዜና ድርጅቶችን ይዘት ማረጋገጥ እና ላማጋራት ፈቃደኛ አልሆነም ማለቱን ተከትሎ ሩሲያ ፌስቡክን ገድባለች።

የዛራ ብራንድ ልብስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ምርት አቅራቢ ድርጅቶች

ግዙፉ የስዊድን ፋሽን ኩባንያ ኤች ኤንድ ኤም በሩሲያ ስራውን ያቆመ ግዙፍ ምርት አቅራቢ ድርጅት ሆኗል። ይህንንም ተከትሎ በርካታ ኩባንያዎች ይህንን ፈለግ ሊከተሉ እንደሚችል ተዘግቧል።

ኤች ኤንድ ኤም በዩክሬን ውስጥ " አሳዛኝ ሁኔታዎችን" ጠቅሶ ስራውን ሲያቆም ናይኪን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ብራንዶች በአሁኑ በሩሲያ ላሉ ደንበኞች ምርት ለማቅረብ ዋስትና እንደማይሰጡ ተናግረዋል።

በሞስኮ ታዋቂው አደባባይ አቅራቢያ ግዙፍ መሸጫ ያለው 'ቡርቤሪ' የተሰኘው ብራንድ "በሩሲያ ውስጥ ትዕዛዞችን ላማድረስ አስቸጋሪ ስለሆነ" ሁሉንም ጭነት አቁሜያለሁ ብሏል።

ሩሲያ በ2021 አምስተኛዋ ትልቅ የአውሮፓ የችርቻሮ ምርቶች ገበያ የነበረች ሲሆን 337 ቢሊዮን የእንግሊዝ ፓውንድ የሚገመት ነው። አንዳንድ ብራንዶች ደግሞ ከተወሰነ ወደ ንግዱ የመመለስ እድል ካለ በሚል ሁሉንም መንገድ ዝግ አላደረጉም።

ለዚያም ይመስላል በርካታ ድርጅቶች ሽያጫቸውን ሙሉ በሙሉ ከማቆም ይልቅ ጉዳዩን "እያጤንን ነው" ወይም "ስራ በማቆም ላይ ነን" እያሉ የሚኙት የሚል አስተያየትም የቀረበው።

ተሽከርካሪ አምራቾች

በሩሲያ ወረራ ምክንያት ወደ ሀገሪቱ ተሽከርካሪዎች ካቆሙት አምራቾች መካከል 'ጃጓር ላንድሮቨር'፣ 'ጄኔራል ሞተርስ'፣ 'አስቶን ማርቲን' እና 'ሮልስ ሮይስ' የተባሉት እውቅ ኩባንያዎች ይገኝበታል። በተጫማሪም የግንባታ መሣሪያዎች አምራቹ 'ጄሲቢ' በሩሲያሁሉንም ሥራዎች አቁሟል።

አሁን መኪኖችን ወደ ሩሲያ ማጓጓዝ ከባድ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም የዓለም ሁለቱ ትላልቅ የባህር ማጓጓዣ ባለቤት ኩባንያዎች 'ኤም ኤስ ሲ' እና 'ሜሪስክ ' ከምግብ፣ ህክምና ቁሳቁሶች እና የሰብአዊ አቅርቦት በስተቀር ሌላ ምርት ለሩሲያ አንጭንም ብለዋል።

እንደ ቮልስዋገን እና ቢኤምደብሊው ያሉ አንዳንድ የመኪና አምራቾች በአንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት የሚገኙ ፋብሪካዎች ላይ ከዩክሬን የሚቀረቡ የመኪና ክፍሎች ባለመኖራቸው ምርታቸውን ለተወሰ ጊዜ ለማቆም ተገደው ነበር።

የህግ አማካሪ ድርጅቶች

ከኮሚኒዝም መውደም በኋላ በሩሲያ ስራ ከጀመሩ ቀዳሚ ዘርፎች መካከል ትላልቅ አማካሪዎች እና የሕግ ኩባንያዎች ይገኙበታል።

ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈፀመችውን ወረራ ተከትሎ አብዛኞቹ ዝምታን መርጠው የቆዩ ቢሆንም መሰረቱ ዩኬ የሆነው 'ኬፒኤምጂ' የተሰኘው አማካሪ ኩባንያ ሃላፊ ጆናታን ሆልት ከማዕቀቡ ጋር በሚናበብ መልኩ ከደንበኞቻቸውን ጋር ያለንን ግንኙነት እየገመገምን ነው ብለዋል።

ይህ ማለት በዩናይትድ ኪንግደም እና በመላው አለም ያሉ አንዳንድ ግንኙነቶችን ማቋረጥ ሊሆን እንደሚችልም ተናግረዋል።

ሌላው 'ኢዋይ' የተሰኘው አማካሪ ድርጅት ማዕቀቡን እንደሚያከብር የገለጸ ቢሆንም በሩሲያ ከሚገኙ ከማንኛቸውም ደንበኞች ጋር ያለውን ግንኙነት አቋርጣለው ወይም አላቋርጥም ብሎ እርግጡን አልተናገረም።

ሌሎች የህግ እና አማካሪ ድርጅቶች የደንበኞቻቸውን ከሩስያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እናጤናለን ብለዋል።

የ'ማክኪንሴ' አማካሪ ድርጅት ስራ አስፈፃሚ ኩባንያው "ከእንግዲህ በሩሲያ ውስጥ ማንኛውንም የመንግስት አካል እንደማያገለግል" በማህበራዊ ሚዲያ ጽሁፍ ላይ አጋርቷል።

ማን ቀረ?

ሩሲያ በማዕቀብ ጎርፍ በምትጥለቀለቅበት በዚህ ሰዓት ተጨማሪ እውቅ ብራንዶች በሩሲያ ስራ እንዲቆሙ ጥሪ እየቀረበላቸው ነው።

ሆኖም ለአንዳንድ ኩባንያዎች ይህንን ማድረግ በጣም ከባድ ነው። በሚቀጥሉት ቀናት እና ሳምንታት ውስጥ ጫናው እየበረታ ቢሄድም በሩሲያ ስራ ማቆም ለነዚህ ድርጅቶች አስቸጋሪ ይሆናል።

የምዕራባውያን ማዕቀቦች ለመቋቋም የሩስያ መንግሥት የሩስያ ንብረቶችን ሽያጭ አግዷል። ይህ በመሆኑ በቅርብ ዓመታት ውስጥ በሩሲያ ውስጥ ስራ የጀመሩ ክባንያዎች ንብረት ሽጦ ሀገር ጥሎ የመውጣት መንገዱ ተዝግቶባቸዋል።